ለሀገሪቱ የትምህርት ጥራት መረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ትኩረት እንደሚያሻ ተገለጸ

72

ጎባ ሚያዚያ 10/2011በሀገሪቱ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በተደረገው ጥረት የተገኘው ውጤት ጥራትንም  ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርና ትኩረት እንደሚሻ ተገለጸ።

“ቅንጅታዊ አሰራር ለትምህርት ጥራትና ቀጣይነት ላለው ልማት!”  በሚል መሪ ሀሳብ መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው  ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት  በባሌ ጎባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በአውደ ጥናቱ መድረክ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተመራማሪ ፕሮፌሰር ድርብሳ ዱፌራ   ባደረጉት ንግግር " በሀገሪቱ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፈን  በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት ተገኝቷል" ብለዋል።

የትምህርት ጥራት ማነስ ግን ፈታኝ ሆኖ መቀጠሉን  የገለጹት ፕሮፌሰሩ በሀገሪቱ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጥራት መውረድ ከዚያ ደረጃ በላይ ለሚገኙ የትምህርት እርከኖች  አስቸጋሪ በመሆኑ ልጆችን ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እንዲዘጋጁ ማድረግ እንደሚገባ አመለክተዋል።

የትምህርት ሰዓታት በአግባብ ያለመጠቀም፣ የመምህራን የስራ ትጋት ማነስ፤ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ወላጅ ኮሚቴዎች  ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣት ሌላው ክፍተት መሆኑን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡  

የሃገሪቱን የትምህርት ጥራትና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማሻሻል ለተዘጋጀው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ስኬት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረትና ቅንጅታዊ ርብርብ እንደሚያሻ  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ መርሃ ግብር መምህር  ዶክተር ወርቁ ነጋሽ እንዳሉት የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ላይ የሚያደረገውን የጥራት ቁጥጥር ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል፡፡

"መንግስት በተለይ በአሁኑ ወቅት በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ እያደረገ የሚገኘውን የጥራት ቁጥጥርና የእውቅና መስጠቱን ሂደት በመንግስት ተመሳሳይ  ተቋማትም ጭምር  ተፈጸሚ ቢያደርግ በሀገር ደረጃ የሚፈለገውን ጥረት ለማምጣት ያስችላል "ብሏል፡፡

"የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በዘርፉ የሚስተዋሉ የአቅርቦት ችግርና በትምህርት አሰጣጥ ሂደት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት ችግሩን ተደራሽ ማድረግ  ትኩረት ሊሰጠው ይገባል " ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና መምህር  ዶክተር ፍርዲሳ ጀቤሳ ናቸው፡፡

ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ለዘርፉ አካላት ብቻ የማይተው መሆኑን በመረዳት  መሳተፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የመዳወላቡ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አቡበከር ከዲርበበኩላቸው "ዩኒቨርስቲው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ በሃገሪቱን  የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማሟላት በሚደረገው ጥረት  የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል "ብሏል፡፡

በአውደ ጥናቱ መድረክ 18 ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ያመለከቱት ዶክተር አቡበከር ልምድ ያላቸው አንጋፋ ተመራማሪዎች ለወጣቶቹ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት እንደሚሆንም ገልጿል፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማሩ ስራ በተጓዳኝ ከ300 የሚበልጡ ማህበረሰብ ተኮር የጥናትና ምርምሮችን ማካሄዱን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ  ከሀገሪቱ የተለያዩ  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራንና  ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም