በያቤሎ ከ1 ሺ 200 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን አደንዛዝ እጽ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በያቤሎ ከ1 ሺ 200 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን አደንዛዝ እጽ ተያዘ
65
ሚያዝያ 10/2011 ከመሀል ሀገር ወደ ሞያሌ ሲጓጓዝ የነበረ ካናቢስ የተባለ አደንዛዝ እጽ መያዙን በሞያሌ ገቢዎችና ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ አስታወቁ፡፡
አስተባባሪው ኢንስፔክተር አለሙ ይመር እንደገለጹት አደንዛዝ እጹ የታየዘው ትናንት በያቤሎ ገቢዎችና ጉምሩክ በመቆጣጠሪያ ሰራተኞች በተደረገ ፍተሻ ነው፡፡
አደንዛዝ እጹን ሲያጓጓዝ የተያዘው የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 - 57519 ኢት ሲኖ ትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ ከስር ለመንገድ ስራ አገልግሎት የሚውል ጠጠር በመጫን ተሸሽጎ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሽከርካሪውና ረዳቱ ለጊዜው ቢሰወሩም ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ኢንስፔክተር አለሙ አስታውቀዋል፡፡
በመቆጣጠሪያ ጣቢያው ሰራተኞች ፍተሻ የተያዘው ይሄው አደንዛዝ እጽ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ወርም በተመሳሳይ በተደረገ ፍተሻ በርካታ ካናቢስ የተባለ አደንዛዝ እጽ መያዙን ከአስተባባሪው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኢንስፔክተሩ እንዳሉት በህግ የተከለከለ አደንዛዝ እጽ ሲያዘዋውር የተገኘ ከአምስት ዓመት በሚበልጥ እስራትና በገንዘብ ያስቀጣል፡፡
የያቤሎ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ህገወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከል ከፌደራል ፣ከኦሮሚያና ከነዋሪው ህዝብ ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡