726 የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞች ለስደት ለተጋለጡ ወጣቶችና ሴቶች በጀመረው የሥራ ዕድል ፈጠራ ኘሮጀክት ተጀመረ

119

ሚያዝያ 10/2011በኢትዮጵያ ለስደት ለተጋለጡ ወጣቶችና ሴቶች የተጀመረው የሥራ ዕድል ፈጠራ ኘሮጀክት 726 የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞችን በአዲስ አበባ አስመረቀ።

ከእነዚህም ተመራቂዎች 439 ሴቶች፣ 287 ወንዶች ሲሆኑ ፕሮጀክቱ የስራ እድልንም ለተመራቂዎቹ ያመቻቻል ተብሏል።

ኘሮጀክቱ ለወጣቶችና ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የመሰደድ ዝንባሌ ያላቸውንና ከስደት ተመላሾችን እንዲሁም ስደተኞችን ጨምሮ ለስደት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ በማድረግ በሰሜንና በመካከለኛው ኢትዮጵያ ያለውን መደበኛ ያልሆነ ስደት ለመከላከል አስተዋጽኦ ማበርከት ነው።

ለተግባራዊነቱ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተነግሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድና አዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴ እንዳሉት የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች  በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ለስራ ዝግጁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በአገር ውስጥም ሠርቶ በመለወጥ ኢ-መደበኛ ስደትንም ያስቀራል ብለዋል።

ምክትል ከንቲባው አያይዘውም ፕሮጀክቱ በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሴቶችና ወጣቶች ላይ እየተወሳሰበ ያለውን ስደትና ገፊ ሀይሎች በመቀነስ ለስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ወይዘሮ ቴሪ ሊዩቲኔን “ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ወደ ትግበራ መግባቱ ዜጎችን ከስደት ተጋላጭነት ከመጠበቁም በላይ የስራ ዕድልን በማመቻቸት እ.አ.አ በ2025 ዓ.ም ልታሳካው ለጀመረችው ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ መዳረሻ አንዱ ፍኖት ነው” ብለዋል።  

ተመራቂዎቹ ከየካ፣ ከአዲስ ከተማ፣ ከአራዳ እና ከቂርቆስ ክፍለ ከተማዎች በመመልመል በጄኔራል ዊንጌት፣ በልደታ እና በምስራቅ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች የ3 ወር ስልጠና እንደወሰዱም ተገልጿል።

ከየካ ክፍለ ከተማ የመጣው ከስደት ተመላሽና ስልጠናውን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው መንገሻ ፋንታሁን  ለኢዜአ እንደገለፀው ከስልጠናው የስራ ዕድል ለማግኘት የሚያስችል ሙያ ባለቤት ከመሆኑም በላይ በተመረቀበት ዘርፍ መቅጠር ከሚያስችሉ ድርጅቶች ጋር ትስስር እንዲፈጥር እንዳገዘው ተናግሯል።

በቆይታቸውም በቆዳ ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍና በብረታ ብረት የስልጠና መስኮች ላይ ያተኮረ ስልጠና እንዳገኙ ታውቋል።

ለዚህም መሳካት ዕገዛና ትብብር ላደረጉ ድርጅቶችና መምህራን የዕውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።

በእያንዳንዱ የሙያ ስልጠና ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎችም ዋንጫና ሰርተፊኬት ተበርክቷል።

ፕሮጀክቱ በተመረጡ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚቀጥል ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም