መንግስት የጸጥታ አካላትን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው---ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው

67

ሚያዝያ10/2011 መንግስት የጸጥታ አካላትን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የፌዴራል ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ተናገሩ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለመላው አመራሮቹና አባላቱ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ።

ስልጠናው ለአመራሮቹና ለአባላቱ ከመጋቢት 9 አስከ ሚያዚያ 9 ቀን 2011ዓ.ም በሶስት  ዙር  ሲሰጥ መቆየቱም ተገልጿል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል እንደሻው ጣሰው በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መንግስት የጸጥታ አካላትን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ኮሚሽነር ጄነራሉ አክለውም፣ አገሪቷ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደምትገኝና ለውጡ ህዝባዊና ህገ-መግስታዊ መሆኑን በመጥቀስ በህዝብ ፍላጎት የመጣው ለውጥ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የጸጥታ አካላት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

ለውጡ በፖሊስ ተቋማት ውሰጥ ስኬታማ እንዲሆንና ወቅቱ የሚጠይቀውን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት  ተቋሙን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፖሊስ አመራሮችና አባላትም የለውጡን ባህሪ ተገንዝበው በተለይም የሰብዓዊ መብቶችን አክብረው በማስከበር ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ኮሚሽነር ጄነራሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን ከምንም በላይ ለሰው ሃብት ልማትና ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን  ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም እንዲሁ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፣ ስልጠናው የአመራሮችንና የአባላትን የማስፈጸም አቅም የማጎልበት አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው መሰል ስልጠናዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል ሲል  የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም