በምስራቅ ጎጃምና ደቡብ ወሎ የማዳበሪያ እጥረት የዘር ስራን እያስተጓጎለ ነው

66

ሚያዝያ 10/2011 በዞኑ ግብርና መምሪያ የግብዓት አቅርቦት ባለሙያ አቶ አድነው ስለሽ እንደገለጹት ለ2011/2012 የምርት ዘመን ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ ነው ።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም 600 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ማዳበሪያ ቀርቦ በዩኔኖች አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እንዲደረስ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ሆኖም " ኤኒ ፒ ኤስ ቦሮን " የተባለው ከ620 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማስገባት ቢታቀድም በአሁኑ ወቅት 160 ሺህ ኩንታል ብቻ መቅረቡንና እጥረት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው እንዳመለከቱት የመጣውን ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎችና አካባቢዎች ለማዳረስ ቢሞከርም የአርሶ አደሩ ፍላጎት በመጨመሩ ችግሩን ማቃለል አልተቻለም።

ተፈላጊው ማዳበሪያ እንዲቀርብ ለሚመለከተው አካል ጠይቀው መልሱን እየተጠባበቁ አንደሆነ ጠቁመው በዞኑ ቀጣዩ የምርት ዘመን ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ የምግብ ሰብል ለማምረት መታቀዱን አስረድተዋል፡፡ 

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ የቀበሌ አምስት  አርሶ አደር ጀማል አህመድ እንዳሉት በተያዘው  ዓመት በሶስት ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ፣ስንዴ፣ ማሽላና ሽምብራ ለመዝራት  ዝግጅት እያደረጉ ነዉ፡፡

ለዚህም ከ6 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እንደሚፈልጉና በወቅቱ ዘርተው ተጠቃሚ ለመሆን ቢያስቡም ማዳበሪያ እተቀረበ አለመሆኑ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላዉ የከላለ ወረዳ አርሶ አደር የሱፍ አሊ በበኩላቸው በሁለት ሄክታር ማሳ ላይ ጤፍ፤ በቆሎና ሌሎች ሰብሎችንም ለመዝራት ማሳቸዉን በማለስለስ ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡

የእርሻ መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ ለዘር ዝግጁ ያደረጉ ቢሆንም የሚፈልጉት አምስት ኩንታል ማዳበሪያ ማግኘት ባለመቻላቸው ስራቸውን እያስተጓጎለባቸው መሆኑን የተናገሩት  አርሶ አደር አቶ የሱፍ አሊ ናቸው፡፡

መሬቱ ያለማዳበሪያ ምርት እንዳማይሰጥ የሚናገሩት አቶ የሱፍ መንግስት በፍላጎታቸዉ ልክ በወቅቱ አቅርቦላቸዉ ከህገ ወጥ ደላሎችና ነጋዴዎች እንዲታደጋቸዉ ጠይቀዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ አለባቸዉ ባዩ " በአርሶ አደሩ ፍላጎት መሰረት በቂ ማዳበሪያ እንዲቀርብ ጥረት ብናደርግም አቅርቦቱ እየዘገዬ ነው" ብለዋል፡፡

ከባለፈዉ ዓመት ልምድ በመውሰድ ቀድሞ እንዲቀርብላቸው  ለሚመለከተዉ አካል  ቢያሳውቁም  በጨረታ መዘግየት፣ የወደብ ቅብብሉ መጓተትና ሀገራዊ የጸጥታ ችግሮች እንዲስተጓጎል ማደረጉን ገልጸዋል፡፡

"በዞኑ የሚፈታ ባለመሆኑ ለአርሶ አደሩ የማይሆን ተስፋ አንሰጥም፤የፊደራል መንግስት በትኩረት ሊሰራ ይገባል፤ያለዉን እንኳ ለማሰራጨት አልፎ አልፎ የሚሰተዋል የጸጥታ ችግር እንቅፋት ሆኖብናል" ብለዋል፡፡

ለምርት ዘመኑ ከታቀደዉ ከ374 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እስካሁን ከ100 ሺህ በታች መግባቱን ጠቅሰው ከደረሳቸውም ውስጥም  50ሺ ኩንታሉ ቀድሞ በሚዘራባቸዉና የመንገድ ችግር ባለባቸዉ ወረዳዎች መሰራጨቱን አመልክተዋል፡፡

በመኸር ወቅቱ በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው 442 ሺህ ሄክታር መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓቶችና የገጠር ፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ መንስግቱ አሰፋ በበኩላቸው በአማራ ክልል ለመጪው የመኸር እርሻ 5ሚሊዮን 300ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ታቅዶ  4 ሚሊዮን 900ሺህ ኩንታል ግዥ መፈፀሙን ገልጸዋል።

እስካሁንም ከ2ሚሊዮን 100ሺህ  የሚበልጠው ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቶ በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ ነው፡፡

ሆኖም ከወደብ በገጠመ የትራንስፖርት እጥረት አርሶ አደሩ ለዘር ወቅት የሚፈልገው " ኤን ፒ ኤስ ቦሮን " የተባለው ማዳበሪያ እጥረት እንዳለ ዳይሬክተሩ አመልክተው " ችግሩን ለመፍታት በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጭምር አቅጣጫ ተሰጥቶ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም