የደደቢት እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ ተራዘመ

57

አዲስ አበባ ሚያዝያ 10/2011በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ሊካሄድ የነበረው የደደቢት እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ ተራዘመ

ሌሎቹ የሊጉ ጨዋታዎች በተያዘላቸው ቀንና ሰዓት መሰረት ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚካሄዱ ይሆናል።

በሊጉ መርሃ ግብር እሁድ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የደደቢት እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታ በደደቢት ጥያቄ መሰረት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገልጿል።

ለዚህም ቡድኑ ተጫዋቾቹ በፋይናንስ ችግር ምክንያት ከሁለት ቀን በፊት ልምምድ ማቆማቸውን ተከትሎ በዚህ ሳምንት ከጅማ አባጅፋር ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ እንዲራዘም ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ጨዋታው ለሌላ ጊዜ ተዘዋውሯል።

ቀሪዎቹ ጨዋታዎች በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት የሚካሄዱ ሲሆን ነገ በ 9፡00 ሲዳማ ቡና ከስሁል ሽረ በሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ድሬዳዋ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ደቡብ ፖሊስ ከወላይታ ድቻ በ9፡00 ክልል ላይ ሲጫወቱ ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይገናኛሉ።

መከላከያ ከፋሲል ከተማ እሁድ በ10፡00 በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጫወቱ መቀለ ሰብአ እንደርታ ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ሐዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 9፡00 ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።

ፕሪሚየር ሊጉን መቀለ ሰብአ እንደርታ በ42 ነጥብ ሲመራ ፋሲል ከተማና ሲዳማ ቡና በእኩል 34 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ይከተላሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ባህርዳር ከተማና ጅማ አባጅፋር ከአራት እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

መከላከያ፣ ስሁል ሽረ እና ደደቢት ከ14 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኮከብ ግብ አግቢነቱን የመቀለ ሰብአ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በ12 ጎሎች ሲመራ ምንይሉ ወንድሙ ከመከላከያ በ11 ጎሎች እንዲሁም አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና በ10 ጎሎች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም