ሙያዊ ብቃትን መሰረት አድርጎ በመስራት ከተገልጋይ የሚነሱ ቅሬታዎችን መቅረፍ ይገባል

56

ሚያዝያ 10/2011 ሙያዊ ብቃትን መሰረት አድርጎ በመስራት ከተገልጋይ የሚነሱ ቅሬታዎችን መቅረፍ እንደሚገባ ተገለጸ::

የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት "ሙያዊ ብቃት ለላቀ የህዝብ ተሳትፎ" በሚል  መሪ ቃል ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች ጋር ዛሬ የፓናል ውይይት አካሄዷል።

በውይይቱም ሙያና ሙያተኛን መሰረት ያደረገ የብቃት ማእቀፍና ተግዳሮታቸው ተዳሰውበታል።

በዚህም "አንድ ባለሙያ ሙያውን በአግባቡ ተወጥቷል" ልንለው የምንችለው ሙያው የሚፈልገውን እውቀትና ክህሎት  በመያዝ ሙያዊ ስነ ምግባሩን በመከተል ለተገልጋይ ፈጣን አገልግሎት መስጠት ሲችል መሆኑ ተነስቷል።

ተቋሙ ባለሙያው በሙያው እራሱን ሊያሳድግ የሚችልበትን ስልጠናዎች እንዲያመቻችለት በማድረግና ክፍተቱን በመለየትም እራሱን ሁልጊዜም ማዳበር እንደሚገባ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ባምላክ እሸቱ ተናግረዋል።

በአገራችን አሁን እየታየ ያለው የሃሰት የትምህርት ማስረጃም በብቃት ማእቀፍ ላይ ትልቅ  ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱ በውይይቱ ተነስቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ከከፍተኛ የትምህረት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ የሙያ ስልጠና መስጫ ማእከሎች አናሳ መሆንና አንዳንድ ተቋማት ላይ የሚመደቡ የስራ ሃላፊዎች የፖለቲካ አቅማቸው ብቻ ታይቶ ስለሚመደቡ በስራቸው ያለውን ባለሙያ የመምራት አቅማቸው አለመመጣጠንም እንደ ተግዳሮት ተነስተዋል ።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚፈለገውን የሙያ ብቃትና ብቁ ሞያተኛ ለመፍጠር በቂ የሆኑ የስልጠና ማእከላት ግንባታ እንደሚያስፈልግና ያሉትም ስልጠና ከሰጡ በኋላ ምንያህል ወደ  ተግባር መለወጥ ይችላሉ የሚለውን መፈተሽ እንደሚገባ የፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ማስረሻ አበበ ተናገረዋል።

በተቋማት ውስጥ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዳይኖር የሰው ሃብት ስራ አመራራችን መቀየር እንዳለበት ገልጸው፤ ስራና ሰሪውን በተገቢው መንገድ ማገናኘት የሚችል አሰራር መዘርጋት አለበትም ተብሏል።

አንድን ተቋም ለመምራት የፖለቲካ አቅም መኖሩ መልካም ሆኖ እያለ በስሩ ያሉ ባለሙያዎች ጋር የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ግን ተቋሙን የሚመራው አካልም ሆነ ባለሙያዎች አንድን ተቋም እና ማህበረሰቡን እንደሚያገለግሉ በማወቅ ሙያዊ ግዴታቸውንና ሙያዊ ስነምግባርን በተላበሰ መልክ መተግበር እንዳለባቸው ደግሞ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማእከል የጥናትና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የዚህ መሰሉ ፓናል ውይይት መካሄዱ በቀጣይ ክፍተቶችን በመለየት መፍትሄ ለማበጀት የሚያስችላቸውና በተቋማቸው ውስጥም ያለውን ክፍተት  ለመለየት ቀስቃሽ እንደሆነላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም