ተሿሚዎቹ ለአገራዊ ለውጥ የነበራቸውን ሚና ሊደግሙ ይገባል-የምክር ቤት አባላት

233

ሚያዝያ 10/2011 አቶ ለማ መገርሳና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አገራዊ ለውጡ እንዲመጣ የነበራቸውን ሚና በአዲሱ የሚኒስትር ሃላፊነታቸውም ሊተገብሩ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ሁለቱን በክልል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን ጨምሮ የሶስት የሚኒስትር ሹመቶችን በአንድ ተቃውሞና በአምስት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

የኦሮሚያና የአማራ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የነበሩትና አሁን ባለው አገራዊ ለውጥ የመሪነት ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው  አቶ ለማ መገርሳና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመከላከያና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ተሹመዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የምክር ቤቱ አባላት አዳዲሶቹ ሹመኞች  ቀደም ሲል የነበራቸውን የለውጥ ሚና በተሾሙበት አዲስ ኃላፊነትም መድገም እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ሁለቱም የክልል ፕሬዝዳንቶች የነበሩት አመራሮቹ ለውጡን በመምጣት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱና በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው ባለስልጣናት እንደሆኑ ገልጸው፤ በአዲሱ ኃላፊነትም ያንኑ ስሜትና ሃሳብ በአንድነት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው ነው ያብራሩት።

በዚህም አገሪቷ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታና ሰላምና መረጋጋትን ከግምት ውስጥ በማስገባት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ  የዲፕሎማሲ ዘርፎች ላይ ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ከመከላከያ ሚኒስትርነት ወደ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን የተዛወሩት ኢንጂኔር አይሻ መሀመድም ከሙያቸው ጋር የሚገናኝ በመሆኑ  የተሻለ ውጤታማ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጨዎች መካከል  አቶ አለሙ ገብሬየመከላከያና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሾሙ ሰዎች ሁለቱም ቢሆኑ አሁን በአገር ደረጃ ላይ እየመጣያለውን ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሲደግፉና ሲመሩ የነበሩ ናቸው።

በክልል ደረጃ ከፍተኛ ፖዚሽን ላይ የነበሩ ናቸው። እነዚህ አካላት ናቸው ወደዚህ የመጡት። በፌዴራል ደረጃ ላይ የተጀመረውን ለውጥ ውጤታማ ለማድረግ የቡድን ስራ ነው እንግዲህ ለውጥን መምራት የሚቻለውና የጋራ ስሜት ፈጥረው የጋራ ሃሳብ ይዘው ወደ ተግባር መቀየር የሚችሉ ናቸው። አቶ ገዱ ህዝቡ ሲደግፋቸው የነበሩ የለውጡ አራማጅ ናቸው። አቶ ለማም በክልልም እጅግ ተቀባይነት ያለው በአገር ደረጃም ይህን ለውጥ ማራመድ የሚችሉ ሰዎች ናቸው። ተገቢ ቦታ ነው የተሾሙ የሚል አስተያይት ነው ያለኝ።” ብለዋል

“በአጠቃይ የሚኒስትሮች ሹመት ስናይ እንደ እኔ ወደ ፊትም ተሞክሮ መወሰድ አለበት።  ሁለተኛ አሁን ያለነው በለውጥ ማዕበልና ንቅናቄ ነው። ለውጥ ሲመጣ ለውጥን የሚደግፉ እንዳሉ ሆኖ ለውጡን የሚጎትቱም የሚያደናቅፉም ጽንፈኛ ኃይሎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ለውጥን ከማጠናከር፣ ለውጥ የሚመራው አካል ጋር ተያይዞ ኢንጂኔር አይሻም ከመከላከያ ሚኒስቴር የበለጠ የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው ቢሰሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ የሚል እይታ ነው ያለኝ”የሚሉት አቶ ዮሴፍ ዳማይ ናቸው።