ኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ልምዷን ለኔፓል ልታስተዋውቅ ነው

57

 አዲስ አባባ  ሚያዝያ  10/2011 ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያስመዘገብችውን ውጤት ተከትሎ ኔፓል ልምዷን ለመቅሰም እንደምትፈልግ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዩንድራ ያዳቭን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኔፓል አቻቸውን ዩንድራ ያዳቭን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋ።

በውይይታቸውም ሁለቱ አገራት ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚቻልበት ምቹ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት አድርጓል።

በተለይም የኔፓል መንግሥት ከኢትዮጵያ መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ፖሊሲ ስኬቷን መቅሰም እንደምትችል ውይይት ተደርጓል።  

ይህም የኔፓል መንግሥት በጤና ዘርፍ ልምድ ለመቅሰም ያሳዩትን ፍላጎት ተከትሎ መሆኑ ነው የተገለጸው። 

በእነዚህም ርዕሰ ጉዳዮች ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ልዩ ረዳት አቶ አብይ ኤፍሬም ገልጸዋል።

ኔፓል የኢትዮጵያን የፌዴራሊስም ሥርዓት ተሞክሮና በሃይል ዘርፍ ደግሞ ከውኃ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ ልምድ ለመቅሰምም ፍላጎት አሳይታለች።

በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይም በቀጣይ በጋራ እንዴት መሥራት እንደሚቻል የመሪዎቹ የውይይት ትኩረት ነበር ተብሏል።

ኢትዮጵያም በሁለቱ አገራት መካከልም ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የደቡብ ለደቡብ ትስስሩን ማጎልበት እንደምትሻ ገልጻለች። 

ኢትዮጵያና ኔፓል በቅኝ ያልተገዙ፣ የበርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ መሆናቸውም አገራቱን ያመሳስላቸዋል።

ኢትዮጵያና ኔፓል የሁለትዮሽ ግንኙነታችውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1970ዎቹ ቢሆንም ግንኙነቱ የሚጠበቀውን ያክል አላደገም።

በማደግ ላይ የምትገኘው የደቡብ እስያዋ 'ኔፓል' 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም