የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ ውሎው በክልል አመራርነት ሰፊ ልምድ ያላቸውን ሚኒስትሮች ሹሟል

99

አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2011 በክልል አመራርነት ሰፊ ልምድ ያካበቱት አቶ ለማ መገርሳና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአገር መከላከያ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ ውሎው በክልል አመራርነት ሰፊ ልምድ ያላቸውን አዳዲስ ሚኒስትሮች ሹመት አጸደቀ።

አቶ ለማመገርሳ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  እንዲሁም የአገር መከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን ኢንጂነር አይሻ መሐመድን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አድርጎ ሹሟቸዋል።

ዛሬ የአገር መከላከያ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ለማ መገርሳና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ማን ናቸው?

የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ለማ መገርሳ ዋቆ  ዕድሜ 44፣ የትውልድ ቦታ ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ሲሬ ወረዳ፣ የትምህርት ዝግጅት የመጀመሪያ ዲግሪ በኢኮኖሚክስ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሶስተኛ ዲግሪ በሰላምና ደህንነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመከታተል ላይ ከነበሩ በኋላ በስራ ጫና ምክንያት ያቋርጡ ናቸው።

የስራ ልምዳቸውን በተመለከተ በተለያዩ የአስተዳደር ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን በመንግስትና በድርጅት በተለያዩ ቦታዎች ሰፊ ልምድ አካብቷል። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣የኦሮሚያ ጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ በመሆን ያገለገሉ፤ የአሮሚያ ንግድና ልማት ቢሮ ኃላፊና የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሆኖ ያገለገሉ። አሁን ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በመሆን በማገልገል ላይ የነበሩ ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በለጠ ደግሞ የትውልድ ቦታ ወሎ ዕድሜ 50 ዓመት፣ የትምህርት ዝግጅት የመጀመሪያ ዲግሪ በትምህርት አስተዳደር ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፣ የሁለተኛ ዲግሪ በተቋማዊ አስተዳደር እና ሊደርሺፕ ተመርቀዋል።

የስራ ልምዳቸውን በሚመከለከትም በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች አገልግለዋል። በብአዴን/በአሁኑ አዴፓ በጽፈት ቤት ኃላፊነት ያገለገሉ፤ የአማራ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ፣የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆኖ ያገለገሉ ናቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ደግሞ  የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር ሆነው አገልግለዋል።

ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ከመከላከያ ሚኒስትርነታቸው በፊት የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም