አምባሳደር መለስ ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

70

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2011በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማ ጋር የሁለቱ አገሮችን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማ ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የጠበቀ ወዳጅነት ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል።

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካው ዘርፍ ያላትን መልካም ግንኙነት የሁለቱ ህዝቦችን ህይወት የሚለውጥና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ውጤት እንዲያመጣ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ ጠቁሟል።

ሁለቱ አገሮች እስካሁን የፈረሟቸውን በልዩ ሁኔታ የመተባበር ስምምነቶች እንዲተገበሩና ለውጤታማነታቸው በቅርበት ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባም ማመልከታቸውን መግለጫው ገልጿል።

አምባሳደር መለስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት ከፖለቲካ ግንኙነት ባለፈ የሁለቱን ህዝቦች በጋራ የመበልጸግ ራዕይ እውን ለማድረግ አጽንኦት ሰጥታ ትሰራለች።

ኢትዮጵያ በሁለቱ አገሮች በልዩ ሁኔታ የተፈረሙ የትብብር ስምምነቶችም ተጫባጭ ለውጥ እንዲያመጡና የሁለቱ አገሮች ህዝቦችን ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ መሸጋገሯን የጠቀሱት አምባሳደር መለስ፤ ሁለቱ አገሮች ለአፍሪካ ቀንድ ሠላም የማይተካ ሚና እንዳላቸው መግለጻቸውን የፕሬስ መግለጫ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም