በምዕራብ ጎንደር ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በመጭው የመኽር እርሻ ሥራ እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሰራ ነው

50

ጎንደር ሚያዚያ 9/ 2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን ወደ አካባቢያቸው በመመለስና በማቋቋም በመጭው የመኽር እርሻ ሥራ እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የህዝብ ደህንነትና ሰላም ግንባታ መመሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለኢዜአ እንደተናገሩትበአካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተሰራ ነው፡፡

ዞኑ ሰፊ የእርሻ ቦታ ያለውና ሰሊጥና ጥጥ በብዛት የሚመረትበት አካባቢ በመሆኑ የእርሻ ስራ ሳይጀመር ተፈናቃዮችን በፍጥነት መልሶ ለማቋቋም  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ከመመለስና መልሶ ከማቋቋሙ በፊት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የማጠናከር ሥራ መሰራቱንና በእዚህም በሁለቱም በኩል መልካም አቀባበል ማግኘታቸውን የገለጹት ኃላፊው በዞኑ ከሚገኙ ሰባት ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከህዝብ ጋር በተደረገው ውይይት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ እንዳሉት የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም የዞኑ ህዝብ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ በተደረሰ ስምምነት መሰረትም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ ተሰብስቧል፡፡

በዞኑ 45 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቁመው እስካሁንም በመተማና በቋራ ወረዳዎች ከ300 በላይ አባውራዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ተፈናቃዮችን መልሶ ለማደራጀት በተደረገው እንቅስቃሴ ከህዝብ ከተገኘው ድጋፍ በተጨማሪ ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡

በገንዳ ውሃ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙት አቶ አጠቃ አወቀ በበኩላቸው የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋምና ወደቀያቸው ለመመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት ደስተኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

የመኸር እርሻ ጊዜ ሳያልፍ ወደአካባቢያቸው ተመልሰው ለግብርናው እንዲዘጋጁ ለማድረግ መንግስት የጀመረውን ሥራ እንዲያፋጥንም ጠይቀዋል፡፡

" ከቀያችን ተፈናቅለን ወደመከላከያ ካምፕ ከመጣን ሦስት ወር አለፈን፤ በቅርቡ ትመለሳላችሁ ስንባል ደስ ብሎናል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዘነቡ እሸቱ የተባሉ ተፈናቃይ ናቸው።

ወደቀያቸው ሲመለሱ ያለፈውን ይቅር በመባባል አዲስ ሕይወት መመስረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በጊዜያዊ መጠለያ ያሉበት ሁኔታ በስነልቦናቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው የአካባቢው አስተዳደር ፈጥኖ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል፡፡

በዞኑ የገንዳ ውሃ ከተማ የህዝባዊ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አለባቸው በላይ በበኩላቸው ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በሚችለው አቅም ለተፈናቃዮች ድጋፍ እደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የተፈናቀሉት ወደአካባቢያቸው ሲመለሱ መልካም አቀባበል በማድረግና ያለፈን ቂምና ቁርሾ በመተው የነበረን ቀድሞ ወንድማማችነት ለማስቀጠል የሁሉም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል"፡፡

በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋትና ግጭት የሰው ሕይወትና ንብረት የወደመ ሲሆን ከ2 ሺህ በላይ ቤቶችም መቃጠላቸውን ከዞን አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም