ፍቃድ ለተከለከሉ የምግብ አምራች ድርጅቶች በፌደራል ባለስልጣኑ መሰጠቱ ተገቢ አይደለም

92

አዲስ አበባ ሚያዝያ 09/2011 በአዲስ አበባ የምግብ የመድሃኒትና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ ለተከለከሉ የምግብ አምራች ድርጅቶች በፌዴራሉ የምግብና የመድሃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ መሰጠቱ ተገቢ ባለመሆኑ በአስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ የፌደራል ዋና ኦዲተር አሳሳበ።

የኢትዮጵያ የምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ደህንነትና ጥራት ቁጥጥር አፈጻጸም በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ላይ የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አና የተቋሙ አመራሮች ውይይት አካሂደዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር ዋና ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደገለጹት የአዲስ አበባ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ፍቃድ ለማግኘት የሚያስችሉ መስፈርቶችን ባለመሟላታቸው  ፍቃድ ያልተሰጣቸው ድርጅቶች አሉ።

ሆኖም አነዚሁ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል።

በባለስልጣኑ አመራሮች በኩልም  በክልሎች የሚሰሩ ድርጅቶች የፌደራል ባለስልጣን እንዲቆጣጣር በአዋጅ የተሰጠው ስልጣን በመሆኑ ነው የሚል ምላሽ መሰጠቱን ገልጸዋል።

አቶ ገመቹ እንደገለጹት ድርጅቶቹ ፍቃድ የተሰጣቸው በአዲስ አበባ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የተከለከሉበት ትክክለኛ ምክንያት ሳይጣራና መስፈርቶቹን ማሟላታቸው ሳይረጋግጥ በመሆኑ ትክክለኛ ምላሽ አይደለም።

በመሆኑም ባለስልጣኑ ችግሩን በሚገባ ፈትሾ በድርጊቱ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ባለስልጣኑ  በኦዲት ግኝት ላይ የተሰጡ ግብዓቶችን በመጠቀም የተፈጸሙ ስህተቶችን በአስቸኳይ እንዲያርም አሳስቧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሀመድ የሱፍ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ከተቋቋመበት አላማ አኳያ የምግብ፣የመድሃኒትና ጤና ተቋማትን፣ የባለሙያዎችን የብቃት ማረጋገጫ መስጠትና መቆጣጠር፣ የግብዓቶችን ጥራት ደህንነትና ፈዋሽነትን በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅና ማበልጸግ ይኖርበታል።

ሆኖም እነዚህ ተግባራት በአግባቡ ባለመከናወናቸው በአገሪቱ በተደጋጋሚ  የአተት በሽታ መከሰቱ፣ የታሸጉ ውሃዎች ከጥራት ደረጃ በታች መሆናቸው፣ በተለያዩ ወቅቶች የሕብተሰቡን ጤናና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ሲከሰቱ ተጠያቂ አካላት ያለመለየትና ሌሎች ችግሮች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

በአገሪቱ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በምግብና ውሃ ወለድ በሽታዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡም አክለዋል።

በመሆኑም ባለስልጣኑ ጥብቅ የሆነ ክትትልና የቁጥጥር ስርዓት በማዘጋጀትና የውስጥ ኦዲት አቅሙን በማጠናከር ሊሰራ እንደሚገባ አቶ መሀመድ ተናግረዋል።

ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ባለስልጣኑ በምግብ፣መጠጥና መድሃኒቶች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ 37 ድርጅቶች ላይ የድህረ ፍቃድ አንስፔክሽን ሳይከናወን የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱ፣ ፍቃድ ሳይኖራቸው ምግብ የሚያመርቱና የጥራት መቆጣጠሪያ ላብራቶሪ  ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች መኖራቸውን፣ ምግብ በሚጓጓዝበት ወቅትና ገበያ ላይ የዋሉ ምግቦችን ደህንነትና ጥራት የማረጋገጥ ስራ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ያለመውሰዱ በኦዲት ክትትል መረጋገጡም ተነስቷል።

ከውጭ አገር የሚገቡና አገር ውስጥ ለሚመረት ማንኛውም ምግብ የምግብ ስርዓት ምዝገባ የተዘረጋ ቢሆንም የምግብ ምዝገባ እየተከናወነ አለመሆኑን ፣የምግብ ንግድ ድርጅት የድርጅቱን ስምና አድራሻ ድርጅቱ በሚገኝበት ቦታ መለጠፍ ላይ በተደረገ ክትትል በናሙና ተመርጠው የታዩ ድርጅቶች የውጭ ማስታወቂያ ያለመለጠፋቸውና በተመዘገቡበት አድራሻ ያለመገኘታቸውም ሌሎች ችግሮች ናቸው።

የምግብ አምራቾች ቶሎ ሊበላሹ የሚችሉ ምግቦችን አቀማመጥ፣ በሚታሸግበትና በሚጓጓዝበት ወቅት በተገቢው ሙቀት መጠን ማስቀመጥና ማጓጓዝ ላይ ፣ ከምግብ ጋር ቀጥተኛ ንኪኪ ያላቸውን ሰራተኞች ንጽህና አጠባበቅ ላይ ባለስልጣኑ ተገቢውን ክትትል እንደማያደርግም ነው የተጠቆመው።

የምግብ ጥራት  ምርመራ ላብራቶሪዎችን በማደራጀት የተሟላ የምግብ ደህንነት ጥራት ቁጥጥር የማይደርግ መሆኑ፣ ምርመራ የሚደረገው ከምግቦች በዘይትና ጨው ላይ መሆኑ፣ በኬላዎች የሚገኙ መርማሪዎች በእይታ በሚያደርጓቸው ምርመራ የሚያግዙ የተሟሉ መሳሪያዎች ያለመኖርም በኦዲቱ የታዩ ግኝቶች ናቸው።

ከክልሎች ጋር ለመስራት ሊደረጉ የሚገባቸውን ስራዎች ባለስልጣኑ የማያከናወን መሆኑንና ከምግብ ጋር ባዕድ ነገሮችን የመቀላቀል ወንጀሎችን ለመከላከል በህብረተሰቡ በኩል ንቅናቄ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የምግብ የመድሃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄራን ገርባ በሰጡት ምላሸ ባለፈው አመት  በተካሄደው የኦዲት ግኝቶቹ መሰረት በርካታ የማስተካከያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ  ከ40 ሺህ በላይ የምግብ ተቋማት ላይ የኦዲትና ምርመራ ስራዎች መከናወናቸውን በባለስልጣኑ በኩልም በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ 70 በመቶ የሚሆኑት የምግብ አምራቾች አስመጪዎችና አከፋፋዮች ላይ የድህረ ፍቃድ ኢንስፔክሽን መከናወኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም  በወተት፣ በዘይትና ለውዝ ምርቶች ላይ በተደረጉ የቁጥጥር ስራዎች የጥራት ችግሮች ለመፍታት ባለመቻሉ በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን አንስተዋል።

የምግብ ምዝገባ ስርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩንና እስካሁንም 1 ሺህ 520 የምግብ ምርቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።

እንደ ወይዘሮ ሄራን ገለጻ አድራሻቸው የማይታወቅና ከባለስልጣኑ ዕውቅና ውጭ ሌላ ስራዎችን ሲያከናውኑ የተገኙ 205 ድርጅቶች ላይ የፍቃድ መሰረዝና ሌሎች አርምጃዎች ተወስዷል።

የምግብ ተቋማት የፍቃድ ምዝገባን በኤሌትሮኒክስ የታገዘ ለማድረግ የሙከራ ሰርዓት መጀመሩንና ሙሉ ለመሉ ተግባራዊ ሲሆን ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማስፈን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ባለስልጣኑ የሚጠቀማቸው ላብራቶሪዎች በቂ ባለመሆኑ የምግብና የመድሃኒት ላብራቶሪዎችን  የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም የመግቢያና የመውጫ ኬላዎች አካባቢ መሰረተ ልማቶች የተሟሉ ባለመሆኑ ላብራቶሪዎችን ማደራጀት ፈታኝ መሆኑን አክለዋል።

ሁሉም የምግብ አይነቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የአቅም ውስንነት በመኖሩ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን 30 የምግብ አይነቶች መለየታቸውንና በአሁኑ ወቀት 23 የምግብ አይነቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለጹት የምግብ ላብራቶሪዎች  የስልጠናና የምርምር ማዕከላትን የሚያካትት የሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ ፕሮጀክት ተቀርፆ ግንባታ ለማከናወን ሂደት ላይ ነው።

ይህም በምግብ ደህንነትና ጥራት ላይ ያሉትን ችግሮች በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በምግብ፣መጠጥና መድሃኒቶች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ለ37 ድርጅቶች ላይ የድህረ ፍቃድ አንስፔክሽን ሳይከናወን የብቃት ማረጋገጫ የተሰጠው የሕብረተሰብ ደህንነት ላይ ሊያስከትሉ ከሚችሉት ጉዳትና ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ምግቦችና መሰረታዊ መድሃኒቶች  አንጻር በስጋት ተኮር መለየት ቀይ፣አረንጓዴና ቢጫ ተብለው በመከፈፋል የ3ኛ ወገን የጥራት ማረጋጋጫ መስፈርት ካሟሉ የድህረ ፍቃድ ቁጥጥር ሳይደረግ የብቃት ማረጋጋጫ የመስጠት አሰራር መሰረት መሆኑን አብራረተዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በ2010 ዓ. ም 112 ሺህ የምግብ ተቋማት መኖራቸውንና  በፌደራልና በክልሎች  ከ40 የማይበልጡ ተቆጣጣሪዎች ብቻ መኖራቸውንም አንስተዋል።

የአቅም ውሰንነት ችግሩን ለመቀነስም ተቋማት ራሳቸውን መቆጣጠር የሚችሉበትን የውስጥ ቁጥጥር ስርዓት ሙሉ ለመሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተይዟል ብለዋል።

ባዕድ ነገሮችን መቀላቀልን ለመከላከል ንቅናቄ ለመፍጠር እየተሰራ ሲሆን በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። 

የመግቢያና መውጫ ኬላዎቸ ላይ ላብራቶሪዎች ባይደራጁም ባለሙያዎች ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ፍተሻ የማድረግ ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።