በህግ አምላክ!...በህግ! ሊደመጥ የሚገባው የዜጎች ጩኸት!

163


በሃብታሙ አክሊሉ(ኢዜአ)

ጓደኛዬ ተወልዶ አድጎበት፣ ጎልማሳነትን እያጣጠመ የሚገኝበት ሰፈሩ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ሳር ቅጠሉ ያውቀዋል። ተራ አስከባሪዎች፣ ቀን በሌዎች፣ ያለ ስራ አውደልዳዮች፣ ያደባባይ ሻይና መብል አቅራቢዎች፣ የዕድር ጥሩምባ ነፊዎች፣ የታክሲ ረዳቶች፣ የአውቶቡስ አውታንቲዎች፣ አልጋ አከራዮች፣ ጉሊት ቸርቻሪዎች እረ ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው የሰው አይነቶች ያውቁታል። ይሁን እንጂ ለጓደኛዬ ይህ እውቅና ምን አተረፈለት፤ ምንም። በሰፈር መታወቁ ረብ የለሽ እንዲሆን ያደረገው ጉዳይ ምንድነው? አትሉም! ባለፈው ሳምንት ነው እንግዲህ አንድ ምሽት ብዙም መሸ ሊባል በማይችልበት ከምሽቱ 2 ሰአት ተኩል ሳይሞላ እንደተለመደው ወደ ቤቱ ሊገባ የሰፈሩን አቅጣጫ እንደያዘ ከየት መጡ የማይባሉ የዝርፊያ ቀበኛ ጎረምሶች እሱ ወዳለበት አቅጣጫ እየጮሁ መጡ። ጓደኛዬ ተደናገጠ፤ የቁጥራቸው መብዛት የደቦ ስራ ሰርተው የሚመለሱ የአንድ አነስተኛ ወረዳ ነዋሪዎችን እንጂ በተደራጀ ዘረፋ ተግባር ላይ የተሰማሩ አይመስልም። እንደመጡ ጓደኛዬ ላይ የዱላ ውርጅብኝ ያወርዱበት ገቡ። “ኪሴ ውስጥ ያለ ነገር በሙሉ ውሰዱ ነገር ግን እባካችሁ አትደብድቡኝ። በህግ አምላክ! በህግ! ሲልም ተማፀናቸው ” ሰሚ ግን አላገኘም። የቻሉትን ያህል ደበደቡት፤ ከዚያም ጓደኛዬ ራሱን ስቶ ወደቀ። ሞባይልን ጨምሮ ኪሱ ውስጥ የነበሩ ገንዘቦች እና ሌሎች ነገሮችን በሙሉ ዘርፈውት እብስ አሉ።

እንደው ለማለት ያህል አነሳሁ እንጂ በህይወት የመኖር ህልውናውንም አሳጥተውትስ ቢሆን! ወደ ቀልቡ ሲመለስም ራሱን በደም ርሶ፣ ልብሱ በጭቃ ተለውሶ አገኘው። በድብደባው የደቀቀ ሰውነቱ ህመም እረፍት ቢነሳውም በህይወት ለመትረፉ ፈጣሪውን አመሰገነ። የሆነውን ሁሉ ለማስመዝገብ ባቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ሄደ። የደረሰበትን በሙሉ አንድም ሳያስቀር በዝርዝር ተረኛ ለነበሩ ፖሊሶች አስረዳቸው። ምንም ሳይመስላቸው ቃሉን ተቀበሉት። አንዳችም ጠብ የሚል ነገር ሳይፈጥሩለት ያለምክንያት አመላለሱት። ‘ሲጀመር አትቀደም እንጂ ህግ ያለ መስሎሃል’ ስትል እህቱ የነገረችው ትዝ አለው። ውሎ አደረ ነገር ግን ምንም ፍንጭ ሊያገኝ አልቻለም። አውቆ የተኛን… ሆነና ነገሩ አንዳንድ ፖሊሶች የዘረፋ ድርጊት ተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል በሃሜት ደረጃ ሲሰማ ለቆየው እውነታ ጓደኛዬ አንዳች አስረጂ ነገር አገኘለት።

ድሮ ድሮ አንድ ህገ ወጥ ተግባር ሊፈፅም የነበረን ሰው ‘በህግ አምላክ! በህግ’ የምትለዋ መልዕክት ያንን ድርጊት እንዳይፈፅምና ህግ በመተላለፉ ሊደርስበት ከሚችለው ማንኛውም ቅጣት ትታደገው ነበር። አሁን አሁን ግን እንኳን በህግ አምላክ ተብሎ አይደለም የህግ አስከባሪ አካል መሳሪያውን እንዳነገተ ቢመጣ አሌ የሚለው የለም። ከላይ በተተረከው የጓደኛዬ ትርክት ውስጥ ብዙዎችን ማየት ይቻላል። ህግ ይጠብቀኛል፤ ህግ በዕለታዊ እንቅስቃሴዬ ከሚገጥሙኝ መብት ተጋፊዎች ይታደገኛል፤ ህግ ህይወቴንም ንብረቴንም በጉልበት ከሚነጥቁ ይከልለኛል፤ ብለው ከቤት ወደ ዕለት ተግባራቸው የሚሰማሩ ዜጎች ቁጥር አያሌ ናቸውና።

ከተራው ዜጋ አንስቶ እስከ ምሁራን ‘የህግ የበላይነት ይከበር’ እያሉ በየጊዜው ቢጮሁም ሰሚ ያገኙ አይመስልም። ህግ አለማስከበሩ ራሳቸውን ለተለያዩ አላማዎች ያስገዙ ቡድኖች ሰዎችን ከመግደል ከገዛ ቀያቸው እስከ ማፈናቀል አድርሷቸዋል። በከተሞችም ከተራ ዝርፊያ አንስቶ በቡድን ተደራጅቶ በመሳሪያ አስፈራርቶ ግለሰቦችን አልፎ ተርፎም ተቋማትን ጥሪት አልባ እስከ ማድረግ እያደረሳቸው ይገኛል። መንግስት ህግን በማስከበሩ ረገድ አላስፈላጊ ትዕግስትን እያሳየ ይገኛል። የመንግስት ትዕግስት ደግሞ ለህግ ደፍጣጩ ከመጤፍም የሚቆጠር እንዳልሆነ እያየን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሚያዝያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም እትሙ ‘መንግስት ይታገስ እንጂ አይልፈስፈስ!’ በሚል ባወጣው ርዕሰ አንቀፅ ላይ የመንግስትን መታገስ ከአቅመ ቢስነት የቆጠሩ አካላት እንዳሉ አሳይቷል። እንዲህም ይላል “ህግ ማስከበርና የህግ የበላይነት በልመና ተግባራዊ አይሆንም። አንዳንዴ ከ’በህግ አምላክ’ በላይ መሄድን የሚጠይቁ ህግ የሚፈቅዳቸው እርምጃዎችም አሉ።” ይላል። እዚህ ጋር መንግስት ከዜጎቹ ደህንነት ሊበልጥበት የሚችል አንዳችም ነገር የለምና ትዕግስቱን ቀነስ በማድረግ አስተማሪ እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባ መልዕክቱ እንደተላለፈ ልብ ይሏል።

ህገ ወጥ ተግባራት በልካቸው ተገቢውን ምላሽ እያገኙ እስካልሄዱ ድረስ መንግስትስ ዜጎቹን በወጉ እንዴት ሊያስተዳድር ይችላል? ሌላው ቀርቶ የህግ የበላይነት በማይከበርበት ሃገር ላይ የራሱ የመንግስት ህልውና አደጋ ላይ ላለመውደቁ ምን ዋስትና አለው? በቅርቡ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ‘ሂውማን ራይትስ ዎች’ ‘Abiy’s First Year as Prime Minister’ በሚል ርዕስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአንድ አመት ቆይታ አስመልክቶ ባወጣው የስምንት ነጥቦች መመዘኛ ሪፖርት ላይ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት የህግ ትምምን ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ አስቀምጧል። አንደኛው የማህበረሰብ ክፍል በሌላኛው የህግ ጥሰት ሲፈፀምበት መንግስት በሃገሪቱ ህግ መሰረት ትክክለኛውን እርምጃ ይወስድ ዘንድ ሪፖርቱ ጠይቋል። ‘The government needs to take urgent steps to restore law and order where it has broken down.’ ብሏል በምህፃረ ቃሉ (ኤች አር ኤም) በመባል የሚታወቀው የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም። የህግ የበላይነትን ቶሎ ወደ ተግባር መመለሱ አብይ ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም ሪፖርቱ አፅንኦት ሰጥቶታል።

ዜጎች ‘በህግ አምላክ’ ሲሉ ህግ በተቃራኒው ሲቆም ስርአት አልበኝነት እንዲነግስ ያደርጋል። የሃገርም ሆነ የዜጎች ደህንነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል። የመንግስት ስርአትም በህግ መመራቱን ያቆምና ‘መክሸፍ’ እንደ ሃገር ሊያጋጥመን ይችላል። በደርግ ዘመነ መንግስት በተለያዩ ሃላፊነቶች ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ “Ethiopia: A Country on the Brinks” በተሰኘ ርዕስ በፃፉትና በተለያዩ ድረ ገፆችና ማህበራዊ ሚዲያዎች በተሰራጨው ፅሁፋቸው የሃገሪቷ ደህንነት ከጊዜ ወደጊዜ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን አስቀምጠዋል። አቶ ዳዊት ይህንን ፅሁፋቸውን አስመልክተው ከቢቢሲ አማርኛ ቋንቋ ዘጋቢ ጋር ባደረጉት ቆይታ “…የሃገሪቱ የደህንነት ሁኔታ ስንመለከት አንድ ሃገር ውስጥ በነጻነት መንቀሳቀስ የማይቻልበት ሁኔታ ነው ያለው። እንደዚህ አይነት ነገሮች ደግሞ የሚፈጠሩት እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ማዕከላዊ አፍሪካ ባሉ የከሸፉ ሃገራት ነው። በግለሰብ ደረጃ ስንመለከተው ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በስጋት ነው የሚኖረው። ሲወጣም ሆነ ሲገባ በስጋት ውስጥ ሆኖ ነው።” ስለሆነም መንግስት የህግ የበላይነቱን በማስከበሩ ረገድ ግራ ቀኝ የሚልበት አንዳች ነገር መኖር እንደሌለበት ከመልዕክቱ ለመረዳት ይቻላል።

በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር የነበሩት አቶ መሳይ ከበደ ‘Assessing the One Year of Abiy’s Premiership’ በሚል ርዕስኢትዮጵያ ኦብዘርቨርበተሰኘ ድረ ገፅ ላይ ባወጡትፅሁፍ የአብይ መንግስት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበውን ያህል በርካታ ዜጎችን ከመፈናቀል አደጋ ሊታደጋቸው አለመቻሉ እንደ ወቀሳ ሊነሳበት እንደሚችል አስቀምጠዋል።“A persistent complaint against Abiy’s government is the inability to prevent massive displacements of people, often proceeded by bloody conflicts between ethnically diverse people sharing a regional space. Yet, blaming Abiy for these setbacks is a misplaced assessment in that it is a one-sided view. True, the protection of peace and the basic rights of people is the major responsibility of the state…” ፅሁፉ ሲቀጥልም ምንም እንኳን ወቀሳው ያንድ ጎን እይታ ቢሆንም መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበርና ዜጎችን ከተለያዩ የህግ ጥሰቶች የመጠበቅ ሃላፊነትን ለሌላ አካል ሊሰጠው እንደማይችል አስረግጧል።

መንግስት በተናጠል በግለሰብ ላይ እንዲሁም በዜጎች ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ ለሚገኙ የህግ ጥሰቶች ባፋጣኝ ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ ሊያስታግሳቸው ይገባል። የመንግስት ሆደ ሰፊነት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ህዝብን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና መፈናቀል የዳረጉ አጉራ ዘለሎች የህግ ጥሰቱ በተፈፀመበት ቅፅበት አስተማሪና ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። ከላይ በአስረጂነት ፅሁፋቸው የተጠቀሱ ምሁራንም ሆኑ ተቋማት መንግስት የህግ የበላይነትን ጠንከር ብሎ እስካላስከበረ ድረስ ለቀጣዩ ትውልድ የፈረሰች ሃገርን ሊያወርስ እንደሚችል በተለያየ ሁኔታ አስቀምጠዋል።

ለሁለት ቀናት ሃገራዊ የለውጥ ሂደቱ ያለበትን ደረጃና የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገም ለውይይት ተቀምጦ የነበረው የኢህአዴግ ምክር ቤት የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የነበሩ ክፍተቶችን በግልፅ የለየ ውይይት ማድረጉን ከውይይቱ በኋላ ካወጣው መግለጫ ለመረዳት ይቻላል። ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ መንግስት ህግን የማስከበር ወሳኝ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አስቀምጧል። ከዚህም በተጨማሪ ክልሎችና የየአካባቢው የአስተዳደር አካላት የህግ የበላይነት እንዲከበር የየራሳቸውን ግዴታ መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ምክር ቤቱ በመግለጫው አፅንኦት ሰጥቶታል። ለህግ የበላይነት መከበር መንግስት ቁርጠኛ መሆኑንም መግለጫው ይነግረናል። ዜጎችም ቃል ወደ ተግባር ተተርጉሞ መመልከትን በጉጉት እየጠበቁ መሆኑንም በየጊዜው ከሚያንፀባርቁት ሃሳብና ድርጊት ለመረዳት ይቻላልና ለተግባራዊነቱ የሁሉም ወገኖች ርብርብ ወሳኝ ነው።

መንግስት በቅርቡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን ተከስቶ የነበረውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋት በብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ በአከባቢው ሰላም እንዲሰፍን ያደረገበት አካሄድ ይበል የሚያሰኝ ነው። ድርጊቱ ዳግም በሌሎች አካባቢዎች እንዳይከሰት የራሱ አዎንታዊ ሚና ይጫወታልና። በከተሞች ነዋሪው በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ የሚያደርጉ የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን በማጠናከር በርካታ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል። የፀጥና የደህንነት ተቋማቱ ህብረተሰቡን ከጎኑ በማድረግ የተናጠልም ሆነ የቡድን ወንጀል ፈፃሚዎችን የህግ ተጠያቂ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ‘የዘገየ ፍትህ ከቀረ ይቆጠራል’ ነውና ብሂሉ ከላይ በጓደኛዬ ላይ የደረሰው የፍትህ መጓደል በሌሎችም ላይ እየደረሰ በመሆኑ መንግስት በፍጥነት የህግ የበላይነትን በማስከበር ሊፈታው ይገባል፤ ምክራችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም