የምክር ቤቱ ስብሰባ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንደነበረ አጋር ድርጅቶች ገለጹ

79

አዲስ አበባ ሚያዝያ 09/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ያካሄደው ስብሰባ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንደነበረ አጋር ድርጅቶች ገለጹ።

አጋር ድርጅቶቹ በስብሰባው መሳተፋቸው በአገራዊ ጉዳዮች ላይሀሳባቸውን በነጻነት ለመስጠት እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል።

የስብሰባውን መጠናቀቅ ተከትሎ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ሊቀመንበር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ አሻድ ሊሀሰን፣ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አደም ፋራህ፣ የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ-መንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እና የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ አወል አርባ በስብሰባው የነበራቸውን ተሳትፎ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።  

የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ሊቀ መንበር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አጋር ፓርቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉ ሲሆን ስብሰባው ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ ነበር።

አጋር ድርጅቶቹ በስብሰባው ላይ ያላቸው ሀሳብ በነጻነት የመግለጽ ዕድል እንደነበራቸው የተናገሩት አቶ ኦርዲን ድርጅቶቹ ከዚህ በፊት ሲካሄድ እንደነበረው ታዛቢ ሳይሆኑ እንደአባል ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በስብሰባው የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ልምድ እንዳገኘበት አቶ ኦርዲን ገልጸዋል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ የጎላ ተሳትፎ እንደነበረው የገለጹት አቶ ኦርዲ ስብሰባው በቀጣይ የሚኖሩ አቅጣጫዎችንና ያሉ ተግዳሮቶችን ለማወቅ እንዳስቻለውም ተናግረዋል።

እንዲሁም አጋር ድርጅቶች በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በድምጽ ባይሳተፉም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቅጣጫ ለመያዝ የሚያስችል ሀሳብ መሰንዘራቸውን ገልጸዋል።


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው የኢህዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ የተወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ተናግረዋል።


በምክር ቤቱ ስብሰባ የአጋር ድርጅቶች አመራሮች በአገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች የራሳቸውን ሀሳብ በነፃነት የገለጹበት መድረክ እንደነበረም አብራርተዋል። 

እንደ አቶ አሻድሊ ማብራሪያ በምክር ቤቱ ስብሰባ መሳተፋቸው ወደፊት አገራዊ ውህደት በመፈጸም አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችልና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በነጻነት ሀሳባቸውን እንደገለጹ ተናግረዋል።

የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፤ አጋር ድርጅቶች መሳተፋቸው በክልላቸው ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለመግለጽ ያስቻለ ነበር።

በተለይ በአገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ በሱማሌ ክልል ተግባራዊ ለማድረግ ከምክር ቤቱ ስብሰባ ጠቃሚ ግብዓቶችን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ውሳኔ መሰረት በኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ድርጅታቸው ተሳታፊ እንደሆነም ገልጸዋል።

በስብሰባው አጀንዳ ላይ አጋር ድርጅቶች በነጻነት ሀሳባቸውን መግለጽ እንደቻሉ የገለጹት አቶ ኡሞድ በተለይ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ አወል አርባ እንዳሉት፤ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ አጋር ድርጅቶች ድምጽ እንዲኖራቸው ያደረገ ስብሰባ ነበር።

የፌዴራል ስርዓቱን ማዕከል ባደረገ መልኩ አጋር ድርጅቶች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊ የሚሆኑበት ጉዳይ መነሳቱን ገልጸዋል።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ሚያዝያ 7 እና 8 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ አገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ክልሎችና የየአካባቢው መዋቅር ህገ መንግስታዊ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስታውቋል።

የህግ የበላይነትን በማስከበር በኩል ያሉ ክፍተቶችን በማረም ሁሉም ህገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበት ገልጿል።

ምክር ቤቱ ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎችንና ያለፉትን ወራት የዕቅድ አፈፃፀም በጥልቀት በመገምግም አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባው አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም