ችሎቱ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

103

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2011ከትናንተ በስቲያ ጀምሮ ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩ በከባድ ሙስና የተጠረጠሩ 21 ግለሰቦች ላይ የተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ላይ ብይን ለመስጠት ለከሰዓት በኋላ ቀጥሮ ይዞ የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ ከመድሃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ና ከውሃ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከ20 በላይ ተጠርጣሪዎች በችሎቱ ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በአቶ ኃይለስላሴ ቢሆን መዝገብ የሚጠሩ የመድሃኒት ፈንድ  አቅርቦት ኤጀንሲ የቀድሞ ሰራተኞች፣ በአቶ ተስፋዬ ብርሃኑ መዝገብ የተያዙ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስራ ሃላፊዎችና በአቶ አታክልት ተካ መዝገብ ስር የተካተቱት የውሃ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት የተለየ የስራ ኃላፊነት የነበራቸው ናቸው።

ተጠርጣሪዎች በጉዳያቸው ላይ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ክርክር ሲያደርጉ ነበር።

በተቋማቱ ላይ የነበረው ምርመራ ከሁለት ወራት በፊት መጀመሩን የገለጸው  አመልካቹ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ የምርመራ ሂደቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው መጣራት ካለበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።

ተጨማሪ ሰነድ አሰባስቦ ማገናዘብ፣ የፎረንሲክ ምርመራና የትርጉም ስራዎች፣ ተጨማሪ የምስክር ቃል መቀበልና ተያያዥ ስራዎች እንደሚቀሩት የገለጸው ፖሊስ፤ ወንጀሉ ከባድና ውስብስብ በመሆኑ ምርመራውን ለማድረግ ተጨማሪ የ14 ቀናት እንዲፈቀድለት ዛሬ ጠዋት ለዋለው ችሎት መጠየቁ ይታወሳል።

ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸውና በተከላካይ ጠበቃቸው እንዳስረዱት ደግሞ 'መንግስት  ምርመራ ተጣርቶ ነው ተጠርጣሪዎች የተያዙት' ብሎ መግለጫ መስጠቱን ገልጸው ለምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ለፖሊስ ሊፈቀድለት አይገባም ሲሉ ተከራክረው ነበር።

ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ያቀረባቸው ምክንያቶችም በቂ አይደሉም፣ ተጠርጣሪዎችም በእስር ላይ ቆይተው ምርመራው እንዲካሄድ የሚያስገድዱበት አግባብ የለም፤ ስለዚህ የዋስትና ህገ መንግስታዊ መብታችን ይከበር ሲሉም ጠይቀዋል።

አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበትን ተቋም ከለቀቁ ከ5 ዓመታት በላይ  ያስቆጠሩ እንዳሉ በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎቹ በመንግስት ተቋማት እጅ የሚገኙ ሰነዶችን አያሸሹም፣ በአዲት ግኝት ሰነዶች ማሰባሰብና ማመሳከር ስራ ተዕጽኖ የሚያሳድሩበት አግባብ እንደማይኖርም ገልጸዋል።

ፖሊስ እቀበላቸዋለሁ ያላቸውን ምስክሮች ማንነት ባልገለጸበት ሁኔታም በተጠርጣሪዎች የማስፈራራት፣ የማባባልና ማስረጃ የማሸሽ ስጋቶች አሉኝ ማለቱ ተገቢ  እንዳልሆነ አስረድተዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎች ከነበራቸው ከፍተኛ የስራ ሃላፊነት አኳያ ከፖሊስ የበለጠ ለምስክርነት የምፈልጋቸውን ግለሰቦችን የሚያውቁ በመሆኑ ምስክሮችን ያባብላሉ፣ ያስፈራረራሉ፣ የምናሰባስባቸውን ሰነዶች እንዲጠፉ ጫና ያሳድራሉ  በማለት ዋስትናውን ተቃውሟል።

የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ድርጊትምከባድ፣ ውስብስብና ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል በመሆኑ ችሎቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርግለት ጠይቋል።

ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ የዋስትና ጊዜውን ውድቅ አድርጎ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ሚያዚያ 23 ብሔራዊ በዓል በመሆኑ በማግስቱ ለሚያዚያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም