የደንበኞች ጥያቄ መቀነስ በሥራዬ ላይ ጫና ፈጥሮብኛል- ብራና ማተሚያ ድርጅት

153

አዲስ አበባ ሚያዝያ 09 /2011 የደንበኞች ጥያቄ እየቀነሰ መምጣት በሥራው ላይ ጫና እየፈጠረበት መሆኑን ብራና ማተሚያ ድርጅት ገለጸ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማተሚያ ቤቱ የመስክ ጉብሽት በማድረግ በድርጅቱ የተሰሩ ሥራዎችን፣መደረግ በሚገባው ድጋፍና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ከአመራሮቹና ሰራተኞቹ ጋር ተወያይተዋል።

ማተሚያ ቤቱ በደርግ ዘመን በ1970ዎቹ ተራመድ በሚል ስም ለሚስጥራዊ ስራዎች ማተሚያ መቋቋሙን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በኋላም በሽሽግሩ ጊዜ በ1986 የመከላከያን የህትመት ፍላጎት ለሟማላትና ገቢ እንዲያስገኝ በማለም በአዲስ መልክ ተቋቁሟል።  

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ደረሰኞች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ መጽሄቶች፣ የባንክ ደብተሮች፣ ካንላደሮችና የማማሪያ መጻሕፍትን በማሳተም ሲያከፋፍል ቆይቷል።

የብራናማተሚያ ቤት የዕቅድና መረጃ ኦፊሰር ወይዘሮ ዓለምነሽ ወልደየስ የማተማያ ቤቱን እንቅስቃሴ ሲገልጹ እንዳሉት፤ ማተሚያ ቤቱ የአገሪቷን የህትመት ፍላጎት ለሟማላት ባለፉት ግዚያት የተንቀሳቀሰ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወደህ ስራው እየተቀዛቀዘ ነው።

ለአብነትም በ2007 ዓ.ም ይገኛል ተብሎ የታቀደውን ገቢ 92 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ አስታውሰው በ2010 ዓ.ም  ግን 155 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ማግኘት የተቻለው 104 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አንስተዋል።   

ይህም የእቅዱን 67 በመቶ ብቻ ነው ማሳካት የቻለው። በዚህም በፊት ከነበሩት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ገቢ መሆኑን ነው ኦፊሰሯ ያስረዱት።    

እንደ ወይዘሮ ዓለምነሽ ገለጻ በ2011 ዓ.ም በአጠቃላይ ከህትመት ዘርፉ ይገኛል ተብሎ ካታቀደው ገቢ ውስጥ የብራና ማተሚያ ድርጅት ድርሻ 13 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው።   

የህትመት ቴክኖለጂው በየጊዜው መለዋወጥ፣የደንበኞች ፍላጎትና የማተሚያ ቤቱ አቅም አለመጣጠን፣ አንዳንድ የመንግሥትና የግል ተቋማት ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን ወደ ህትመት ስራ መግባታቸው እንደ ተግዳሮት ተጠቅሰዋል።  

በተለይ የደንበኞች ትእዛዝ መቀዛቀዝ ትልቅ ማነቆ መሆኑን ገልጸው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሬ እጥረት የመሳሰሉ ችግሮችም መኖራቸውን አብራርተዋል።  

የግብዓት አቅርቦት ችግር ሌላው የድርጅቱ ፈተና መሆኑን የገለጹት ደግሞ የማተሚያ ቤቱ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያለው መኮንን ናቸው።

ማተሚያ ቤቱ የይዞታ ማረጋጋጫ ካርታ የሌለው በመሆኑ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያዎችን ማድረግ እንዳልቻለ አመልክተው ይህም ድርጅቱ አቅሙን እንዳያሳድግ አድርጎታል ይላሉ።   

የድርጅቱ ደንበኞች በአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት እንደመሆናቸው ሥራ ላይ በዋለው የወጪ ቅነሳ አዋጅ ምክንያት የማተሚያ ድርጅቱ ገቢ እንደቀነስ  ይጠቅሳሉ።  

አቶ ያለው እንደሚሉት በዘርፉ የሰው ኃይል እጥረት እና የሰራተኛ ፍልሰትም ችግር እየሆነ ነው።  

በቋሚ ኮሚቴው የመከላካያ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በበኩላቸው ማተሚያ ቤቱ ጥራት ያለው ሥራዎችን በመስራት የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።  

ድርጅቱ ተወዳዳሪ የሚያደርገው የሰው ኃይል ነው ያሉት አቶ ጴጥሮስ የሰራተኛ ፍልሰት ችግርን ለማቃለል የሰራተኛ ማበረታቻዎችና የሥራ ከባቢን ምቹ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የሥራው ባህሪ ለኬሚካልና ብናኝ የሚያጋልጥ በመሆኑም ሰራተኞች እንዳይጎዱ የሰራተኛውን ደህንነት የሚያረገግጡ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።  

ምክር ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቋሚ ኪሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባም በሰጡት ማሳሳቢያ ፤የይዞታ ማረጋጋጫ ካርታውን በተመለከተ ማተሚያ ቤቱ ከሥራ አመራር ቦርድ ጋር በመሆን መፍትሄ እንዲያገኝ መስራት አለበት።   

በተለይ ገቢን ለማሳደግ ወቅቱ ምን አይነት ህትመቶችን ይፈልጋል? የሚለው ሊታይ እንደሚገባ ጠቁመው ማተሚያ ቤቱ በተፈጠረው ምህዳር ሳቢያ ያቆጠቆጡ መጽሄቶችና ጋዜጦች ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ ውጤታማ እንደሚሆን አመላክተዋል።     

ውል ገብተው ካሳተሙ በኋላ የማይወስዱ ደንበኞች ጋር በመወያየት ችግሩ የሚፈታበትን አቅጣጫ ማስቀመጥ ጠቃሚ ይሆናልም ብለዋል።

ማተሚያ ቤቱ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን መነሻ ካፒታል የነበረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ 158 ሚሊዮን ብር መድረሱን የማተሚያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል።