የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለግብርና ልማት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በየም ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

112

ሚያዚያ 9/2011 ያከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተጎዳ አካባቢያቸው በማገገም ለግብርናው ልማት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በደቡብ ክልል የም ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

በልዩ ወረዳው የተያዘው ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የማጠቃለያ ስነስርዓት ትናንት በፋዕያ ቀበሌ  ተካሂዷል፡፡

በስራው ሲሳተፉ ከነበሩት መካከል  ወጣት አርሶ አደር  ሸሪፍ ዝናብ  በሰጠው አስተያየት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው  ያገገሙ አካባቢዎች በተለይም ምንጮች እንዲጎለብቱና የአፈር ለምነትን በመመለሱ   ምርታማ እንዲሆኑ አስተውጽኦ ማድረጉን ተናግሯል፡፡

" ቀደም ባሉት ጊዜያት የምናመርተው እንደ ሾንከራ አገዳና ሙዝ   በረጅም ጊዜ ምርት የሚሰጡትን ብቻ ነበር  ያለው አርሶ አደሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተፈጥሮ ሃብት ስራ የተጎዳው አከባቢያቸው በማገገሙ በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ቲማቲምና ቃሪያ በማምረት ተጨማሪ ገቢማግኘት እንደጀመሩ ገልጿል ፡፡

አቶ አድማሱ ሹማ  የተባሉ እርሶ አደር በበኩላቸው  ላለፉት ሰባት ዓመታት በተፈጥሮ ሃብት ስራ ላይ መሳተፋቸውን አስታውሰው ከዚህም ተጠቃሚበመሆናቸው   ስራውን ባህላቸው  አድርገው መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡

በህብረት በተመረጡ ተፋሰሶች ውስጥ ከሚሰሩት በተጨማሪ በግል ማሳቸው ላይ ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርታማ በመሆናቸው በዓመት እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር  መቆጠብ እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡

ጠፍተው የነበሩ ምንጮችና ወንዞች  ተመልሰው  ለልማት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም  ጠቁመዋል፡፡

ለእንስሳትም ሆነ ለእርሻ ስራቸው በቂ የውሃ ሃብት  እንዳገኙ ተናግረው  በመስመር ከተከሉት የበቆሎ ምርት   እስከ አርባ ሁለት ኩንታል ምርት መሰብሰ እንደቻሉና ይህም ውጤት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከተጀመረ ወዲህ  መሆኑን ግልጸዋል፡፡

በቀበሌያቸው የተፋሰስ ስራ ከመጀመሩ በፊት ጎርፍ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ጉዳት ያደርስ  እንደነበር የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ መሰለች ወልደዩሃንስ ናቸው፡፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ተግባራዊ በማድረግ ጉዳቱን ማስቀረት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

"እኔ በግሌ በጓሮዬ የተለያዩ አትክልቶችን እያለማሁ ነው " ያሉት አስተያየት ሰጪዋ  በቅርቡ ከቲማቲማ ሽያጭ ብቻ 3ሺ500 ብር በማግኘት ተጠቃሚ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

እስካሁን ያከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተጎዳ አካባቢያቸው መልሶ በማገገም ለግብርናው ልማትና እድገት  ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውአርሶ አደሮቹ  ተናግረዋል፡፡

የየም ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ይሁን አሰፋ "ተፈጥሮ በባህሪዋ ሰው ከጎዳት ትጎዳለች፤ በቃራኒው ከጠበቋት ድግሞ ትጠቅማለች " ብለዋል፡፡

የአካባቢው መልክአ ምድር አቀማመጥ ወጣ ገባ በመሆኑ የተፋሰስ ልማት ስራው የህልውና ጉዳይ ተደርጎ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተሻለለውጥ ማምጣት እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡

"በተፈጥሮ ሃብት ስራችን ተመናምነው የነበሩ የተፈጥሮ ሃብቶቻችን እንዲያገግሙ ማድረግ ተችሏል" ያሉት ደግሞ የልዩ ወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምአገኝ ሙሉ ናቸው፡፡

ኃላፊው እንዳሉት በተያዘው ዓመት በተካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በልዩ ወረዳው ስር ከሚገኙ 31 ቀበሌ ውስጥ 29 ሺ አርሶ አደሮች  ተሳትፈዋል፡፡በዚህምየተሻለ አፈጻፀም ያሳዩ አምስትቀበሌዎች፣አመራሮች፣አርሶአደሮችና ባለሙያዎች የዋንጫና የእውቅና  የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በልዩ ወረዳው የጊቤ ተፋስስን ጨምሮ በ2011 ዓ.ም.  በ33 ተፋሰስ ውስጥ 1ሺ987 ሄክታር መሬት ማልማት እንደተቻለም ተመልክቷል፡፡

በየም ልዩ ወረዳ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከተጀመረ  ስምንት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም