መንግሥት የመዋቅር ጥያቄያችንን በመመለሱ ፊታችንን ወደ ልማት እናዞራለን-የጎሪጌሻና ጋችት ወረዳዎች

72

ሚዛን ሚያዝያ 09 /2011 መንግሥት የመዋቅር ጥያቄያቸውን በመመለሱ ፊታቸወን ወደ ልማት እንደሚያዞሩ የጎሪጌሻና ጋችት ወረዳዎች  ነዋሪዎች ተናገሩ።

ወረዳዎቹ በምዕራብ ኦሞ ዞን በይፋ ተቋቁመዋል።

መንግስት የሕዝቡን ፍላጎትን በማድመጥና ተገቢነቱን በማየት ጥያቄአቸውን በመመለሱ ነዋሪዎቹ መደሰታቸውንና ለአካባቢያቸው ልማት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የጎርጌሻ ወረዳ ነዋሪው አቶ ግራማሽ ባልኮኒ ባለፉት ዓመታት አገልግሎት ለማግኘት እስከ 80 ኪሎ ሜትር በእግር ለመጓዝ እንገደድ ነበር ብለዋል።

ርቀቱ ለወጪና እንግልት ዳርጎን ቆይቷል ያሉት ነዋሪው፣ መንግሥት የወረዳውን ማዕከል በአቅራቢያቸው ማድረጉ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።

የወረዳውን ልማት ለማፋጠን እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል፡፡

በአከባቢው በብዛት የሚመረቱ ቡናና ቅመማ ቅመምን ለገበያ ለማቅረብ የመንገድ ችግር ሊፈታልን ይገባል ብለዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ማሩ ካማራች ያለምንም የጸጥታ ችግር ጥያቄያችን ምላሽ ማግኘቱ የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚያሳይና የሚያስደስት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ጥያቄያችን የወረዳ ማዕከል በቅርበት መደረጉ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊው አገልግሎት ማግኘታችን ነው ብለዋል።

በመሆኑም የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን በቀጣይ እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም አጥተን የነበረውን የመንግሥት አገልግሎት በቅርበት እንድናገኝ መወሰኑ ተገቢ ነው ያሉት ደግሞ የጋችት ወረዳ ነዋሪው አቶ ሻያ ባሩድ ናቸው።

ለአካባቢያያችን ልማትና የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ምላሽ እንደሚሰጥም ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

በወረዳው የልማት እንቅስቃሴ ከመንግሥት ጎን ሆነው የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

የቀድሞ ቤንች ማጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የአዲሱ ምዕራብ ኦሞ ዞን አደረጃጀት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፋጂ ዮሳፒ ሕዝቡ የወረዳ መዋቅር ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ያሳየው ትዕግስት የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

መዋቅሩ ኅብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖማያዊ ግልጋሎቶችን በቅርበትና በፍጥነት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

መንግሥት የወረዳዎቹን መሠረታዊ ፍላጎቶች ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራና ደረጃ በደረጃም ችግሮች እንደሚፈታ ገልጸዋል።

ወረዳዎቹ እንዲጠናከሩ ድጋፍ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው፣መንግሥት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት ሕዝቡ ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የቀድሞ የቤንች ማጂ ዞን ለሁለት የተከፈለ ሲሆን፣ምዕራብ ኦሞና  ሸኮ ቤንች በሚባሉ ዞኖች ተሰይመዋል።

በምዕራብ ኦሞ ዞን ሥር የሚገኙት አዲሶቸ ወረዳዎች 25 ቀበሌ አሏቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም