የተጎጂ ምስክሮችን ደህንነት ጠብቆ በፍርድ ሂደት የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ነው

74

አዲስ አበባ ሚያዝያ 09/2011 የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂ ምስክሮችን ደህንነት ጠብቀው በፍርድ ሂደት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ለመስራት ተስማሙ።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፣የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖችን ጨምሮ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰሩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

ይህ ስምምነት  በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለተጎዱ ምስክሮች  በቂ ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያግዝም ነው የተገለጸው።

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግምክትል ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና በዜጎች ላይም  ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።

ይህን ወንጀል ለመከላከል መንግስት የጸረ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር አዋጅ ቁጥር 909/2007 በማውጣት ወደ ስራ ገብቷል።

ይሁንና ይህ አዋጅ ውጤታማ ባለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በመሻሻል ሂደት ላይ ነው ብለዋል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል የመንግስት ሃላፊነት ብቻ ባለመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት በተለይ የተጎጂ ምስክሮች ያለምንም ፍርሃት በፍርድ ሂደቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ማገዝ ተገቢ ነው ብለዋል።

የፍርድ ሂደቱም ረጅም ጊዜ መውሰዱ ሌላው ተግዳሮት ነው ብለዋል ዶክተር ጌዲዮን።

ስምምነቱን የተፈራረሙ የህግ አስፈጻሚና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የተጎጂ  ምስክሮቹ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ የተሻለ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማጠናከር ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎች በፍርድ ሂደት ደህንነታቸው ተጠብቆ ውጤታማ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማስቻል የመግባቢያ ሰነዱ ዋና ዓላማ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም