ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከታይም መጽሔት ተጽእኖ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ ሆነዋል

232

አዲስ አበባ ሚያዝያ 09/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከታይም መጽሔት የ2019 ዓመት 100 ተጽእኖ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ ሆኑ

ታይም መጽሔት ዛሬ ይፋ ባደረገው የ2019 የፈረንጆች ዓመት 100 የዓመቱ የተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ በመሪዎች ዘርፍ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አካቷል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ጊዜ አንስቶ ዶክተር አብይ አህመድ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ሌሎች መስኮች ያካሄዱት ለውጥ ከአገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት ያስቸራቸው መሆኑ ነው ለመጽሔቱ ምርጫ መሰረት።

በአሁኑ ሰዓት የሚታዩ ግጭቶች፣መፈናቀሎችና የህግ የበላይነት ማስከበር ጉዳይ በእስካሁኑ የስልጣን ቆይታቸው የገጠሟቸው ዋንኛ ፈተናዎች ናቸው።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተጨማሪ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂን ፒንግ፣የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር    ኢምራን ካን፣ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎዛ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ የሮማው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በታይም መጽሔት የ2019 የፈረንጆች ዓመት 100 ተጽእኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሰዎች ናቸው።

ከአርቲስቶች መካከል አሜሪካውያኖቹ ዘፋኞች ቴይለር ስዊፍትና ሌዲ ጋጋ፣ አሜሪካዊው የፊልም አክተር ድዌይን ጆንሰን፣ሜክሲኳዊቷ የፊልም አክተር ያሊትዛ አፓሪቺዮና የደቡብ ኮሪያው “ባንግታን” ቦይስ የሙዚቃ ባንድ ቡድን አባላት ከተጽእኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።

ግብጻዊው የሊቨርፑል ክለብ ተጫዋች መሐመድ ሳላህ፣አሜሪካዊቷ የእግር ተጫዋች አሌክስ ሞርጋን፣ አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ሬብሮን ጀምስ፣ አሜሪካዊው የጎልፍ ተጫዋች ታይገር ውድስና ደቡብ አፍሪካዊቷ የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ካስተር ሴሜኒያ ደግሞ በስፖርቱ ዘርፍ የተካተቱ ሰዎች ናቸው።

የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግና የቅድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ሚሼል ኦባማም ሌሎች በታይም መጽሔት ተጽእኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችለዋል።

የታይም መጽሔት በየዓመቱ የተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችን ስም ዝርዝር ማውጣት ከጀመረ የዘንድሮው ለአሥራ ስድስተኛ ጊዜ ሲሆን በዓለም ዙሪያ በመብት ተከራካሪነት፣ በፈጠራና በሌሎችም ስኬት ደረጃ የተዋጣላቸው ያላቸውን ግለሰቦች ይሰይማል።