የጥላቻ ንግግሮችን ከማስተጋባት ይልቅ የሚያፋቅሩ ሐሳቦችን በማንፀባረቅ ለአገራዊ አንድነት መሥራት ይጠበቅብናል- የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

60


ሐዋሳ ሚያዚያ 9 ቀን 2011 የጥላቻ ንግግሮችን  ከማስተጋባት ይልቅ የሚያፋቅሩ ሐሳቦችን በማንፀባረቅ ለአገራዊ አንድነት መሥራት እንደሚያስፈልግ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ ፡፡

ምሁራኑ ከኢዜአ  ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ እንዲጠላሉ ከሚያደርጉ ንግግሮች በመታቀብ፤ ለአገራዊ አንድነት በጋራ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል።

በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ  ኮሌጅ ኃላፊ ዶክተር ዳኜ ሽብሩ የጥላቻ ንግግር የአንድን ቡድን ወይም የቡድን ተወካይ ዘር፣ ሐይማኖትና ሌሎች ማንነቶች መሰረት ያደረገ ክፉ ሀሳብና ድርጊት መሆኑን ያስረዳሉ።

በሁለት ወገኖቸ መካከል ቂም በቀልና ግጭት የሚቀሰቅስ ፤ የአገርን ደህንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል አብራርተዋል ፡፡

አንዳንድ ምሁራን የጥላቻ ንግግር በማስተጋባት ላይ መሰማራታቸውን ያስታወሱት ምሁሩ፣ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ላይ የተጨካከኑበትና መልካም እሴቶቻቸው  እንዲሸረሸሩ  እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል ፡፡

ምሁራን በኅብረተሰቡ ውስጥ ባላቸው ተቀባይነት በሚናገሯቸውና በሚፅፏቸው ሐሳቦች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ዶክተር ዳኜ ገልጸዋል ፡፡

የጥላቻ ንግግሮችን ከማስተጋባት ይልቅ፤ ፍቅርና አንድነትን ልንሰብክ ይገባል ብለዋል ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሙሉ ጌታ፤  ምሁራን ዕውቀትን ማካበት ብቻ ሳይሆን ጥበብንም ሊጎናፀፉ እንደሚገባ ገልጸው፤ ከአንደበታቸው የሚወጡ ቃላት በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት  መገንዘብና ማስተዋል ያስፈልጋል  ይላሉ፡፡

ከምሁራን አንደበት የሚፈለቁ ሐሳቦች በሙሉ ትክክል ናቸው ብሎ ማሰብና በተመሳሳይ ሚዛን ላይ ማስቀመጥም ተገቢ እንዳልሆነም ገልጸዋል ፡፡

ምሁራን ጥላቻን ወደ ፍቅር የመቀየር ኃላፊነታቸውን መወጣት  እንደሚጠበቅባቸውና እርስ በርስ ከሚያነታርኩ ጉዳዮች ይልቅ፤ አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል ፡፡

መልካም የሚመስሉ ነገር ግን  የሚጎዱ ነገሮችን ለይተው ማሳየት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህርት ፀደንያ ሰለሞን በበኩላቸው በአገሪቱ የሚታዩ  የፖለቲካ ቀውሶች መነሻቸው የጥላቻ ንግግሮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከተማሪዎቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ፍቅርና አንድነትን በመስበክ ተፅዕኖ ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ምሁሯ፤ የጥላቻ ንግግሮች የተስፋፉበት ምክንያት  በጥናት ሊለይና ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ ምሁራን ሀሳባቸውን  የሚያካፍሉበት ምቹ አጋጣሚ መፈጠሩን የገለጹት ደግሞ የሶሺዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊው አቶ ዳግም ዳዊት ናቸው፡፡

አጋጣሚውን ለመልካም ነገር መጠቀም ከተቻለ የተሻለ ነገር ለመፍጠር  እንደሚያስችል የተናገሩት አቶ ዳግም፤ በዚህም ሐሳብን በማንሸራሸር ወደ ኅብረተሰቡ የበሰለና ጠቃሚ ሐሳብ ይዞ መቅረብ ይገባል ብለዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም