ለእስራኤል የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ አባላትና ለኬንያው ሄሊኮፕተር አብራሪ ሽኝት ተደረገ

65

ሚያዝያ 9/2011 በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ላለፉት ሦስት ቀናት የተሳተፉት የእስራኤል የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ አባላትና የኬንያው ሄሊኮፕተር አብራሪ በደባርቅ ከተማ ሽኝት ተደረገላቸው፡፡

የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት የእስራኤል የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ አባላትና የኬንያው ሄሊኮፕተር አብራሪ በቅንጅት ባደረጉት ርብርብ እሳቱን ማጥፋት ተችሏል፡፡

በተለይ የብርጌዱ አባላት ቃጠሎ በደረሰበት ተራራማ ቦታ በእግር ጭምር በመጓዝ ከሄሊኮፕተር አብራሪው ጋር በፈጠሩት የሬዲዮ ግንኙነት ስኬታማ እሳት የማጥፋት ስራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ አበባው እንዳሉት የብርጌዱ አባላት ሄሊኮፕተሩ የሚውል ነዳጅና ውሃ እሳቱ ወደአለበት አካባቢ በቅርብ ርቀት እንዲቀርብ ምክረ ሃሳብ በመስጠት የእሳት ማጥፋት ምልልሱን በቀን ከ 5 ወደ 8 ጊዜ ከፍ እንዲል በማድረግ ውጤታማ ስራ ሰርተዋል፡፡

"በፓርኩ የደረሰውን የእሳት ደጋ ለመቆጣጠር ባደረጉት ጠንካራ ርብርብም የዞኑ አስተዳደርና የፓርክ ጽህፈት ቤቱ በደባርቅ ከተማ አሸኛኘት አድርጎላቸዋል" ብለዋል፡፡

በሽኝት ስነ ስርአቱ ላይ 10 አባላት ላሉት የእስራኤል የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ አባላትና ለኬንያው ሄሊኮፕተር አብራሪ የመልካም ሥራ አፈጻጸም የእውቅና ምስከር ወረቀትና የጃኖ ባህላዊ አልባሳት ስጦታ የተበረከተላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

"ስጦታውም ላደረጉት ድጋፍ መስጋ ከማቅረብ በላይ በቀጣይም ጠንካራ ግንኙነት ፈጥሮ በጋራ ለመስራት ያስተሳስራል" ብለዋል፡፡

የብርጌዱ አባላት ወደፊትም ፓርኩ ላይ የእሳት ቃጠሎ ቢነሳ በቀላሉ መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል በእስራኤልና በኢትዮጵያ መንግስት የጋራ ስምምነት የፓርኩን ስካውቶች በእሳት አደጋ መከላከል ሙያ ለማሰልጠን ቃል መግባታቸውን አቶ አበባው ተናግረዋል፡፡

በፓርኩ የደን ሀብት ዙሪያ የእሳት መቆጣጠሪያና መከላከያ መስመሮችን የመቀየስና የተጠናከረ የጥበቃ ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመተግበር እንዲቻልም የብርጌዱ አባላት በቀጣይ ለፓርኩ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

"በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ከአመድ ለበስ የረመጥ ቅሬትና በሁለት ቦታ ከሚታየው ጭስ በስተቀር የሚነድ ነበልባል እሳት የለም" ያሉት ኃላፊው ሄሊኮፕተሩዋ በዛሬው እለት ለቅኝት ስራ ብቻ የአንድ ቀን ቆይታ እንደምታደርግ አስታውቀዋል፡፡

ይህም ድንገት የሚነሳ እሳት ካለ ፈጥኖ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።  

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ዳግም በተቀሰቀሰውና ላለፉት ተከታታይ ቀናት በዘለቀው የእሳት ቃጠሎ በፓርኩ 400 ሄክታር በሚሸፍን የጓሳ ሳር ላይ ጉዳት እንደደረሰ መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡

በ'ለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮ ይገኙበታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

አሁን ላይ ጠንከርያለጭስየሚታየውበፓርኩሦስትቦታዎችብቻነው" ያሉትባለሙያውጭሱንምሙሉለሙሉለማጥፋትርብርብእየተደረገመሆኑንነው

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም