በመንግስት ከተገዛው 11 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ወደ አገር ገብቷል

106

 አዲስ  አበባ  ሚዝያ  9/2011 በመንግስት ከተገዛው 11 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ወደ አገር መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

ለ2011/2012 የመኸር እርሻ ዝግጅት መጀመሩን ለኢዜአ የገለጹት የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ የግብዓት አቅርቦት፣ የመሬት ዝግጅት፣ የባለሙያና የአርሶ አደር ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ የምርት ዘመኑ ስኬታማ እንዲሆን ከወዲሁ የክትትልና ድጋፍ ተግባሩን እየተወጣ እንደሆነም አመልክተዋል።

ማዳበሪያ ከውጭ ተገዝቶ የሚገባ በመሆኑ በየዓመቱ ከአቅርቦትና ስርጭት ጋር በተያያዘ ችግሮች ያጋጥሙ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አለማየሁ፤ ዘንድሮ ከሌላው ዓመት በተለየ ከጨረታና ከግዢ ጋር በተያያዘ መሻሻል እንዳለም ገልጸዋል።

ይህም መንግስት ከወትሮ በተለየ መልኩ ለግብዓት አቅርቦት ትኩረት እንደሰጠው ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ።

ለጨረታ ይወስድ የነበረውን ጊዜ በማሳጠርና በተመጣጣኝ ዋጋ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ለማድረግ በመንግስት በኩል ሰፊ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ለአርሶ አደሩ በመጪው የመኸር ወቅት ለማቅረብ ከታሰበው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ውስጥ የ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ወይም 11 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዢ ተፈጽሟል ብለዋል።

ከተገዛው ውስጥደግሞ  አምስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ጠቁመዋል።

ይህም ቢሆን ግን ማዳበሪያውን ለማጓጓዝ የትራንስፖርት ችግር መኖሩን ያመለከቱት አቶ አለማየሁ ችግሩን ለመፍታት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

ቀድመው ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች በአፋጣኝ ማዳበሪያው እንዲደርሳቸው ካልተደረገ ኪሳራ እንደሚያጋጥም የጠቆሙት ኃላፊው የህብረት ስራ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዚህ ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

አርሶ አደሩ ከገንዘብ አቅም ጋር በተያያዘ ችግር አጋጥሟቸው ማዳበሪያ ሳያገኙ እንዳይቀሩም በብድር ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በኩል የተቀረጸ 'የቮውቸር ስርዓት' ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በተሰራው ስራም አርሶ አደሩ የሚያቀርበውን 'በጊዜ ማዳበሪያ አቅርቡልን' ጥያቄ ዘንድሮ በአጥጋቢ ሁኔታ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚችልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም