በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በቂ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ተቸግረናል- ተገልጋዮች

62

በአርባ ምንጭ  ሚዝያ 9/2011 በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በቂ የመድኃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ መጀገራቸውን የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ገለጹ።

ሆስፒታሉ የበጀት እጥረትና የሚፈለጉ መድኃኒት በገበያ ላይ መጥፋት ዋነኞቹ  ችግሮቼ ናቸው ብሏል።

የሆስፒታሉ አንዳንድ ተገልጋዮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በመድኃኒት አቅርቦት ችግር  ተገቢውን ግልጋሎት እያገኙ አይደለም።

ከተገልጋዮች መካከል ወይዘሮ ንግስት ተፈራ በሆስፒታሉ በቂ የመድኃኒት ክምችት ባለመኖሩ ከውጭ መድኃኒት ገዝተው ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ለወሊድ አገልግሎት ስመጣ በቀዶ ጥገና መውለድ እንዳለብኝ በሐኪም ከተነገረኝ በኋላ ለሕክምና የሚያስፈልጉኝን የማዋለጃ የእጅ ጓንት፣ ግሉኮስ ፣ የቀዶ ጥገና መቁረጫዎችና መስፊያ ክሮችን እቃዎችና መድኃኒቶችን በሙሉ ከውጭ ለመግዛት ተገድጃለሁ" ብለዋል።

አቶ አሰፋ አመሌ የተባሉ የሆስፒታሉ ተገልጋይ  ከእርግዝና ጋር በተያያዘ በማህፀን አከባቢ ለተፈጠረው ህመም ባለቤታቸውን ለማሳከም ወደ ሆስፒታሉ በመጡበት ወቅት የፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒት ከውጭ እንዲገዙ መታዘዛቸውን አስታውሰዋል።

"ከውጭ የሚገዛው መድኃኒት ውድ ከመሆኑ የተነሳ ለከፍተኛ ወጭ ተዳርገናል"ብለዋል።

የሚመለከተው አካል የሆስፒታሉን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዲፈታም ጠይቀዋል።

አቶ ተስፋየ ሆቶፋ የተባሉ ተገልጋይ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ወባ ታመው በገቡበት ወቅት መድኃኒት በሆስፒታሉ ባለመኖሩ ከውጭ ግዛ በመባሌ  አዘንኩ ይላሉ።

"በሆስፒታሉ በቀላሉ ሊገኙ ለሚችሉ መድኃኒቶች ጭምር ከውጭ እንድንገዛ እንገደዳለን" ያሉት ተገልጋዩ፣ አሰራሩ ላልተፈለገ ወጪ በመዳረጋቸው መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳሙ ኪሮ የበጀት እጥረትና  የመድኃኒት በገበያ ላይ አለመገኘት የችግሩ መንስዔ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሆስፒታሉ በዓመት 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ህሙማንን እንዲያስተናግድ ታስቦ መገንባቱን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፣ ሆስፒታሉ በዓመት ከ3 ሚሊዮን በላይ ሕሙማን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

የሆስፒታሉ ዓመታዊ በጀት 47 ሚሊዬን ብር መሆኑን የገለጹት አቶ አዳሙ የሕሙማንን የመድኃኒት ፍላጎት ለማሟላት ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ እንድሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

በየሩብ ዓመቱ በ2 ሚሊዮን ብር ወጪ መድኃኒት ቢገዛም፤ የተገልጋዮችን ፍላጎት አለማርካቱን ገልጸዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት የበጀት ጥያቄ ለጋሞ ዞን አስተዳደር መቅረቡን አስታውሰዋል።

 መድኃኒት ከሕጋዊ አቅራቢ ድርጅቶች ብቻ እንደሚገዙ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ በሚፈለገው መጠን  በገበያ ላይ እንደማይገኙ አመልክተዋል።

በሪፈራልና ስፔሻላይዚድ ሆስፒታሎች ብቻ የሚገኙ የልብ፣ካንሰርና መሰል በሽታዎች ታካሚዎች መድኃኒት በሆስፒታሉ እንደማይስተናገዱ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም