ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረጉ ጥረቶች ወጣት ምሁራን የማይተካ ሚናቸውን ሊያበረክቱ ይገባል... አቶ መላኩ አለበል

63
ደብረ ብርሃን ግንቦት 26/2010 መንግስት ሰላምና ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ወጣት ምሁራን የማይተካ ሚናቸውን እንዲያበረክቱ የንግድ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ። በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና አገራዊ አንድነት በሚሉ ጽንሰሀሳቦች ላይ በደብረ ብርሃን ከተማ ወጣት ምሁራን በተገኙበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የንግድ ምኒስተሩ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት በቀደሙት ዓመታት በአማራ ክልል በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለተመዘገበው እድገት የክልሉ ወጣት ሙሁራን ድርሻቸው ከፍተኛ ነው። በአገሪቱ ከሚኖረው ሕዝብ 70 ከመቶ ወጣት መሆኑን ጠቁመው፣ ወጣቶች በክልሉ ብሎም በአገሪቱ እድገት ውስጥ አዳዲስ ሀሳብ በማፍለቅ ለለውጥ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የአማራ ክልል በከርሰና በገፀ ምድር ያለውን ሀብት ወደገቢ ምንጭ መለወጥ የሚቻልበት የተሻለ ዕድል መኖሩን ገልጸው፣ ክልሉን ለማልማት በሚደረጉ ጥረቶች በሙያቸው ሊያግዙ እንደሚገባ አመልክተዋል። "ወጣት ምሁራን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና አገራዊ አንድነት ከማጠናከር ባለፈ ባላችው ሙያና ችሎታ ክልላቸውን በመደገፍ የለውጡ አካል ሊሆኑ ይገባል" ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። መድረኩ ወጣት ተመራማሪዎች ”በዴሞክራሳዊ በሔርተኝነትና በአገራዊ አንድነት ” ላይ በቂ እውቀትና ክህሎት ኖሯቸው ነጻና ዴሞክራሳዊ ሀሳብ እንዲያፈልቁ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች ቤሔር ቤሔረሰቦች ጋር ተባብረው በመስራትና ድህነትን በመዋጋት ክልላቸውንና ሀገራቸውን የሚወዱ ወጣቶች እንዲሆኑ የማድረግ ግብ እንዳለውም ሚኒስትሩ አመለክተዋል። በምክክር መድረኩ ላይ ከደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ፣ ከመምህራን ፣ ከጤና ሳይንስና ከቴከኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የተውጣጡ ከ200 በላይ ምሁራን ተሳትፈዋል። በመድረኩም "ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና አገራዊ አንድነት" በሚል ጽንሰ ሀሳብ ላይ ያተኮረ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በመድረኩ የተሳተፉ ወጣት ምሁራንም  ዴሞክራሳዊ በሔርተኝነትን በመጠበቅ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የጎላ ተሳትፎ በማድረግ ለክልሉ ብሎም ለአገር ጥቅም እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም