በሀገሪቱ ተፈናቅለው የነበሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ተመለሱ

83

ሚያዝያ 8/2011በሀገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ተፈናቅለው የነበሩ  ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ከሚሽን አስታወቀ፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር በግጭቱ ተፈናቅለው ወደ ቀያቸው የተመለሱ አባወራዎች በጭልጋ ወረዳ ላዛ ቀበሌ የቤት ግንባታ የማስጀመር ስነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በስነ-ስርዓቱ  ወቅት  የተገኙት  የኮሚሽኑ  ምክትል ኮሚሽነር  አቶ ዳመነ ዳሮታ እንደተናገሩት በሀገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት ከቤት ንብረታቸው ወደ ቀያቸው የተመለሱት ከተፈናቀሉ ሁለት ሚሊዮን 100 ሺህ  ዜጎች ውስጥ ነው፡፡

ቀሪዎቹን ተፈናቃዮች ክረምት ከመግባቱ በፊት በተመሳሳይ ለመመለስ  እየተሰራ መሆኑን አመልክተው" የፌደራልና የክልል መንግስታትም  ርብርብ እያደረጉ ናቸው" ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለተፈናቃዮች ወቅታዊ የእለት ድጋፍ  ከማቅረብ ጀምሮ ሰብአዊ እርዳታው በፍትሃዊነት እንዲዳረስ ተገቢውን ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

" በሀገሪቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ 1 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል " ያሉት ኮሚሽነሩ በመንግስትና በዓለም አቀፍ ለጋሾች ትብብር እንደሚሸፈን አስረድተዋል፡፡

"ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው መርሃ ግብር ማስፈጸሚያም እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግና በክልል መንግስታት ጭምር ድጋፉን ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ ነው "ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚያስተባብሩ 15 ቡድኖች ተቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውን የተናገሩት ደግሞ በሰላም ሚኒስቴር የተመጣጣኝ ልማት ማረጋገጥ ባለሙያ ዶክተር ዮሐንስ ታመነ ናቸው፡፡

በማዕከላዊ ጎንደርም ባለፉት 20 ቀናት 13ሺ የሚጠጉ አባወራዎችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ጠቁመው" ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተፋናቃዮቹን በማቋቋሙ ስራ የቅርብ ድጋፍ እየሰጠ ነው "ብለዋል፡፡

 የጭልጋ ወረዳ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አቡሃይ ጌትነት በበኩላቸው በግጭቱ መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው 2ሺ149 አባወራዎች የመኖሪያ ቤት ለመገንባት የሚያስችል 28ሺህ የቤት ክዳን ቆርቆሮ ለወረዳው መድረሱን ተናግረዋል

 ለአባወራዎቹ እንደ ቤተሰባቸው ብዛት ከ40 እስከ 60 የቤት ክዳን ቆርቆሮ በነፍስ ወከፍ እንደሚሰጥ እና  በባለሙያዎች የግንባታ ቦታ ሽንሸና እንደተካሄደ ገልጸዋል፡፡

ዛሬ የመሰረት ቁፋሮና ግድግዳ የማቆም ስራ እንደተጀመረ የጠቆሙት ምክትል አስተዳዳሪው "እስከዚህ ወር ማብቂያ ድረስ 70 በመቶ የቤቶች ግንባታን ለማጠናቀቅ ርብርብ ይካሄዳል" ብለዋል፡፡

በጭልጋ ወረዳ የላዛ ቀበሌ  አርሶአደር ፈንታሁን ሃይለማርያም በሰጡት አስተያየት "  በግጭቱ ቤት ንብረቴን አጥቼ የመንግስት እጅ ጠባቂ ሆኛለሁ " ብለዋል፡፡

መንግስት ወደ ቀያችሁ ተመለሱ ሲላቸው በፍቃደኝነት መምጣታቸውን የገለጹት አርሶአደር ፈንታሁን ዛሬ  በቀበሌያቸው የመኖሪያ ቤት ግንባታ በመጀመሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

"በግጭቱ 100 ቆርቆሮ የፈጀ መኖሪያ ቤትና ወፍጮ ቤት ጭምር ወድሞብኛል ፤ በአጭር ጊዜ ተቋቁሜ ወደ ቀደመ ሕይወቴ ለመመለስ ጉጉቴ ከፍተኛ ነው "ያሉት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አለምዬ መንግስቴ ናቸው፡፡

በጭልጋ ወረዳ ላዛ በተባለው ቀበሌ ዛሬ በተጀመረው የተፈናቃዮች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ስራ ላይ በጎንደር ከተማ የሚገኙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ አርሶአደሮች፣ የወረዳና የዞን አመራሮች ተሳትፈዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም