በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ተከስቶ የነበረው እሳት ጠፍቷል

85

ሚያዝያ 8/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ተከስቶ የነበረው ሰደድ እሳት ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ለኢዜአ እንደገለጸው በፓርኩ ላይ ተከስቶ የነበረው ሰደድ እሳት በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደገለጹት እሳቱ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካላት ርብርብ ለማጥፋት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በመንግስት እንዲሁም በአካባቢው ማህበረሰብ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የጸጥታ አካላት፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ሆቴሎችና ሌሎችም አካላት የበኩላቸውን ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አውስተዋል።

እሳቱ በፓርኩ ህልውና ላይ የከፋ አደጋ እንዳይፈጥር የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ከኬንያ እና ከእስራኤል የእሳት አደጋ መከላከል ቡድን በማስመጣት እሳቱን የማጥፋት ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ መከናወኑን ነው የገለጹት።

በዚህም ፓርኩ ላይ የተቀሰቀሰው  የሰደድ እሳት በአሁኑ ሰዓት የጠፋ ሲሆን በአካባቢው የሚነድ እና የሚታይ ጭስ እንደሌለም አረጋግጠዋል።

ይሁንና እሳቱ ሃይል ያለው  በመሆኑ ወደ ገደላማው የፓርኩ ክፍል የቀረ እና የተደበቀ እሳት እንዳይኖርም ያለውን ሁኔታ ለመፈተሽ በአሁኑ ጊዜ በበረራ ቅኝት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓርኩ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ እስካሁን 700 ሄክታር የሚሆነው መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል።

በቀጣይም በእሳት ቃጠሎው የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት በባለሙያዎች ጥናት ተደርጎ በቅርቡ ይፋ የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል።

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በአጠቃላይ ወደ 412 ኪሎ ሜትር ስኩየር የሚሸፍን ሲሆን በኢትዮጵያ ብቻ  የሚገኙትን ዋልያ ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የበርካታ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም