ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ውሃ ወለድ በሽታ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ ነው

81

አዲስ አበባ ሚያዚያ 7/2011ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ውሃ ወለድ በሽታ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሳበ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ በሰጡት መግለጫ ተፈናቃዮች ካሉባቸው ወረዳዎች 142 የሚሆኑት ለጎርፍ አደጋ ስጋት ተጋላጭ ናቸው።

በዚህም ሳቢያ በአካባቢው ያሉ ተፈናቃዮች ለውሃ ወለድ በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ በመሆኑና ማሳያዎች በመኖራቸው የሚመለከተው አካል የቅድመ ጥንቃቄ ስራውን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

የውሃ ወለድ በሽታን ከሚያስከትሉ ምክንያቶች አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች መታየታቸውን ጠቁመው በሽታ የመከሰት እድሉ ሰፊ ነው ብለዋል።

በዝናብ ወቅትም የመንገድ መዘጋት ችግር ሊገጥም ስለሚችል ሰብአዊ ድጋፍ ለማቅረብና የሕክምና ባለሙያዎች ተግባር ሊያስተጓጉል ስለሚችል የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

ለተፈናቃዮች የንጽህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማጠናከርና የንጽህና መጠበቂያዎችን በተቻለ መጠን በማጠናከርና የመጸዳጃ ቤቶችን አገልግሎት በማሻሻል ዜጎችን መታደግ ይገባልም ነው ያሉት።

መጪው የበልግና የክረምት ዝናብ የሚዘንብበት ወቅት በመሆኑና በጎርፍ አደጋ ስጋቱ ተጨማሪ መፈናቀሎች እንዳይኖሩ ከወዲሁ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ ለተለያዩ የወረርሺኝ በሽታዎች ተጋልጠዋል ብለዋል።

የተከሰቱት በሽታዎች ተዛማችነታቸውን ለመግታትና አዲስ ተገላጭነትን ለመቀነስ ተፈናቃዮቹ ባሉባቸው ሥፍራዎች ጊዜያዊ የጤና ተቋማት መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

ተጨማሪ 91 የህክምና ባለሙያዎች በአማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በሶማሌ ክልሎች መላካቸውን ጠቁመዋል።

ለተፈናቃይ ወገኖች የሚደረገውን የጤና አገልግሎት ለመደገፍ 27 ተሽከርካሪዎች በየክልሉ መላካቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም