የኦዲት ግኝታቸውን በ2 ወራት መልሱ የተባሉ ተቋማት እስካሁን ወደ ተግባር አልገቡም

124

ሚያዝያ 7/2011 የኦዲት ግኝታቸውን በሁለት ወራት ውስጥ እንዲመልሱ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ባለበጀት መንግስታዊ ተቋማት እስካሁን ወደ ተግባር አለመግባታቸውን ዋና ኦዲተር አስታወቀ።

ባለፈው ወር  መንግስታዊ ተቋማት ከ2002 እስከ 2009 ዓ.ም የተገኘባቸውን 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የኦዲት ግኝት በሁለት ወራት ውስጥ እንዲመልሱ ማሳሰቢያ መሰጠቱ ይታወቃል።

የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለበጀት ተቋማት ኃላፊዎች ሕጋዊ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት በአስተዳደራዊ መፍትሔ ችግሮቻቸውን በሚፈቱባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በውይይቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም በተጠቀሰው ጊዜ ካልመለሱ የፋይናንስና ክዋኔ ኦዲት ችግር ባለባቸው ተቋማት ላይ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተቋማቱና ኃላፊዎችን በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተገልጾ ነበር።

በኦዲት ግኝት ሰፊ ክፍተት አላቸው ተብሎ ከሚጠቀሱ ባለበጀት መንግስታዊ ተቋማት መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቀዳሚ ሆነው ይገኛሉ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደርና ሪፎርም ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ተፈራ፤ ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው ተልዕኮና ባህሪ በስራ ላይ ካሉት የሕግ ማዕቀፎች አለመጣጣም የኦዲት ግኝት መበርታት መንስኤ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ያም ሆኖ ግን መመለስ ያለባቸውን እንዲመልሱ፣ በአሰራር ክፍተት ነው በሚል የማይመልሱትን ደግሞ እንዲያሳውቁ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ምላሽ እያሰባሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ይህን ይበሉ እንጂ የፌዴራል ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ በዚህ ወር መጀመሪያ ለኢዜአ እንደተናገሩት መመለስ የሚችሉት እንዲመልሱ፣ ወይም መመለስ እንደማይችሉ አሳማኝ ምክንያት ያላቸው ምክንያታቸውን እንዲያሳውቁ የተቀመጠውን አቅጣጫ አልተገበሩም ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት ተቋማቱ ገንዘቡን የሚመልሱበትን መርሃ-ግብር እንዲያሳውቁ ቢጠየቁም እስካሁን ቢሮዬ የመጣልኝ ምላሽ የለም ያሉት አቶ ገመቹ፣ ይህ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ አለመዘጋጀታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

እስከ ቀጣዩ ግንቦት ወር መጀመሪያ ሳምንት ድረስ ተጠብቀው ወደ ተግባር ካልገቡ አቃቤ  ሕግ ከዚህ በፊት ከለያቸው ተቋማት ጋር ደምሮ ክስ እንደሚመሰረትባቸውም ነው ያስጠነቀቁት።

ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆኑ ከተደረገባቸው የክፍያ ምክንያቶች መካከል ሕግና መመሪያ ተጥሶ የተከፈለ፣ ከሕግና ስርዓት ውጭ የተከፈለ፣ አስገዳጅ ነገር ሳይኖር ከግዥ ደንብና መመሪያ ውጭ የተደረጉ የግንባታ፣ ግዥና አገልግሎት ቅድመ ክፍያዎችና የጉዳት ካሳዎች፣ ከገቢ ግብርና ደሞዝ ጋር ተያያዞ ያልተመለሱና በጥሬ ያልተሰበሰቡ ገንዘቦች ይገኙበታል።  

አቃቤ ሕግ በ2009 ዓ.ም የኦዲት ግኝትን ብቻ ለይቶ በ15 የፌዴራል ተቋማትና 20 ዩኒቨርሲዎች በድምሩ ለ35 ተቋማት የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በመጀመሪያ ዙር ተጠያቂ ለማድረግ መዘጋጀቱን መዘገባችንም ይታወሳል።

የስምንት ዓመቱ ኦዲት ግኝት በሚሊዮን መለኪያ ሲሰላ በ2002 ዓ.ም 54 ነጥብ 3፣ በ2003ዓ.ም 12 ነጥብ 4፣ በ2004 ዓ.ም 188 ነጥብ 6፣ በ2005 ዓ.ም 333፣ በ2006 ዓ.ም  180 ነጥብ 7፣ በ2007 ዓ.ም 656 ነጥብ 5፣ በ2008 ዓ.ም 397 ነጥብ 8፣ በ2009 ዓ.ም 238ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም