ቆሻሻን ብቻ ሳይሆን ጥላቻን፣ ዘረኝነትንና ክፋትን ከአዕምሮ ማጽዳት ይገባል….በጋምቤላ የጽዳት ዘመቻ ተሳታፊዎች

321

ጋምቤላ ሚያዝያ 6/2011 የአካባቢን ቆሻሻ ብቻ ሳይሆን ጥላቻን፣ ዘረኝነትንና ክፍትን ከአዕምሮ በማጽዳት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መስራት እንደሚገባ በጋምቤላ ከተማ በተካሄደ የጽዳት ዘመቻ የተሳተፉ ነዋሪዎች ገለጹ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን የጽዳት ዘመቻ ጥሪ በመቀበል በጋምቤላ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የጽዳት ሥራ ተከናውኗል።

በጽዳት ዘመቻው ላይ የተሳተፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ተወካይ ዶክትር ሎው አቡፕ እንዳሉት የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ የሚቻለው ጥላቻና ዘረኝነትን ከአዕምሮ አጽድቶ በአንድነት መንቀሳቀስ ሲቻል ነው።

የዛሬው የጽዳት ዘመቻ ዓላማ ቆሻሸን በማስወገድ አካባቢን ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ አዕምሮን ከጥላቻና ከዘረኝነትን በማጽዳት ለሀገር ሰላምና ልማት በጋራ መስራት መሆኑንም አመልክተዋል።

ከህብረተሰቡ ጎን በመሰላፍ አካባቢያቸውን ለማጽዳት መሳተፋቸውን የገለጹት የፌረዳል ፖሊስ ሳጅን ታደለ ዋሴ በበኩላቸው ህሊናን በማጽዳት ለሀገር ሰላም በጋራ መስራት ያስፈልጋል በሚል የተላለፈው ጥሪም በጽዳቱ ለመሳተፍ በተጨማሪነት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

ህዝቡ ጥላቻንና ዘረኝነትን በማስወገድ ለአካባቢው ሰላምና ልማት በጋራ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል።

ሌለዋ ተሳተፊ ወይዘሮ ኛግዋ ፊሊፕ በሰጡት አስተያየት የጽዳት ዘመቻው ህብረተሰቡ ስለአካበቢ ጽዳት ያለውን ግንዛቤ ከፍ ለማረግ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም “ጥላቻንና ሙስናን  እንደ ቆሻሻ በማስወገድ ለጋራ ልማትና ሰላም በአንድነት መስራት እንደሚቻል ለማሳየት ነው” ብለዋል።

”የዛሬው የጽዳት ዘመቻ አካባቢን ከቆሻሻ፣ ውስጣችን ደግሞ ከጥላቻና ከክፋት እናጽዳ″ የሚለውን መርህ እውን ለማደረግ ነው ያሉት ደግሞ በጽዳት ዘመቻው ላይ የተሳተፉት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአካደሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ከተማ ጥላሁን ናቸው ።

ዶክተር ከተማ እንዳሉት ሁሉም ዜጋ አካባቢውን ማጽዳት ብቻ ሳይሆን እርስበርስ ከሚያለያዩ ጉዳዮችና ከጥላቻ ራሱን መከላከል አለበት።

“መቻቻልና መፈቃቀር ካለ እርስ በእርስ በመደጋገፍ የሀገርን ሰላምና ልማት መገንባት ይቻላ” ያለው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የሰላም ፎረም ፕሬዚዳንት ተማሪ ገልገላ ምልኪያስ ነው።

“ልዩነትን ያመጣው ሰው እንጂ ፈጣሪ ሁሉንም አንድ አድረጎ ነው የፈጠረው፤ ልዩነት ፀረ- እድገትና ፀረ-ሰላም መሆኑን ማስተዋል ይገባል” ብሏል ተማሪ ገልገላ ።

በጋምቤላ ከተማ በተካሄደ የጽዳት ዘመቻ የፌዳራልና የክልሉ ጸጥታ አካላት ፣ የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አካላት፣ ነዋሪዎችና የጋምቤላ የኒቨርሲቲ  ሠራተኞችና ተማሪዎች መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው