የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በግብር አሰባሰቡ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መፍታት ይገባል

87

ሐረር ሚያዝያ 6/2011 የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ በግብር አሰባሰቡ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

" ግዴታዬን እወጣለው መብቴን እጠይቃለው " በሚል መሪ ቃል ክልላዊ የግብር ንቅናቄ መድረክ ትናንት በሐረር ከተማ ተካሄዷል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘውዴ ተፈራ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ኮንትሮባንድ፣ ህገ ወጥ ንግድ፣ ሚዛናዊ ያልሆነ የታክስ አወሳሰንና ማጭበርበር በግብር አሰባሰቡ ላይ የተስተዋሉ ተግዳሮቶች ናቸው።

"ታክስ የመሰብሰብ አቅምና የህግ ተገዥነት መዳከም እንዲሁም ግብርን የመክፈል ባህል እየቀነሰ መምጣት ሌላው ተጽዕኖ የፈጠረ ተግዳሮት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ክልሎችን ሳይጨምር በፌዴራል ደረጃ መሰብሰብ የነበረበት 70 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡ በመሰረተ ልማት ግንባታዎችና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

" የዜጎችን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግና ሰላምና ልማትን ለማፋጠን በግብር አሰባሰብ ላይ እያጋጠሙ የሚገኙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በጋራ መታገል ይገባል " ብለዋል።

በተለይ ግብር የመሰብሰበ ባህልን ከማሳደግ ባለፈ ኮንትሮባንድና ህግ ወጥ ንግድን በጋራ መዋጋት እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው አስግንዝበዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየአካባቢው የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የህገ ወጥ ንግድ፣ የደረሰኝ ማጭበርበርና ያለ ንግድ ፍቃድ መነገድ መስፋፋቱንና ይህም በክልሉ በግብር አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ናቸው።

"ችግሩን ለመቀነስ በክልሉ የግብር አሰባሰብ ታክስ ፎርስ በማቋቋም ግብር ከፋዩ ህጋዊ መስመርን ተከትሎ እንዲንቀሳቀስና ግብርን በአግባቡ እንዲከፍል እየተደረገ ነው" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ወደ ህጋዊ መስመሩ ያልገቡ ግብር ከፋዮች በቀጣይ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ታማኝ ግብር ከፋዮችን ለማበረታታትና ግብር በወቅቱ የማይከፍሉትን ለማስተማር ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸው ገቢን በአግባቡ ለመወጣት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ በክልሉ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በክልሉ ታማኝና ከፍተኛ ግብር የከፈሉ 10 ግብር ከፋዮችም የሰርተፍኬትና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከተሸላሚ ግብር ከፋዮች መካከል በከተማው የሚገኘው የምድረ ገነት ሆቴል ባለቤት አቶ ወንድሙ ፈይሳ በየዓመቱ የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ እንደሚከፍሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

"ዘንድሮም 380 ሺህ ብር በወቅቱ ከፍያለው፤ የማበረታቻ ሽልማቱም ሌሎች ግብር ከፋዮች ህጋዊ መንገድን እንዲከተሉና እኔም በታማኝነት የምከፍለውን ግብር እንዳጠናክር ያነሳሳል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ሽልማቱ የሚያበረታታ ቢሆንም የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ከአገልግሎት አሰጣጥና ከአድሏዊ አሰራር ለመውጣት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል" ያሉት ሌላው ተሸላሚ ደግሞ የጣና ሆቴል ባለቤት አቶ ኃይሉ ካሳ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም