ፌዴሬሽኑ ወጣቶች በምርጫ ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ የግንዛቤ መፍጠሪያ ጊዜ ያስፈልጋል እያለ ነው

68

አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2011 የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በ2012 ዓ.ም ለሚደረገው ብሄራዊ ምርጫ ወጣቶች ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ የግንዛቤ መፍጠሪያ ጊዜ ያንሰኛል እያለ ነው።

ፌዴሬሽኑ ወጣቶች ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅት እንዲሁም ከምርጫ በኋላ ያላቸው ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ የመራጮች ግንዛቤ በተለየ መንገድ ለመስራት ጊዜው የተጣበበ እንደሆነበት ገልጿል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት ጽጌሬዳ ዘውዱ ለኢዜአ እንደተናገረችው ወጣቶች በምርጫ ታዛቢነት፣ በመራጭነትና ተመራጭነት ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ግንዛቤ ለመፍጠር ዝግጅት ጀምሯል።

ሆኖም ፌደሬሽኑ የሚወክለውን 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣት ሙሉ ለሙሉ ለመድረስ ለምርጫው የቀረው ጊዜ አጭር በመሆኑ ሊሳካለት እንደማይችል ገምቷል።

በመሆኑም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች በምርጫ 2012 የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን በትክክል እንዲተገብሩ ግንዛቤ ለመፍጠር የቀረው ጊዜ አጭር ነው ብላለች።

እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ገለጻ ወጣቶች መራጮች ብቻ ሳይሆኑ ተመራጮችም በመሆናቸው ከወዲሁ ዝግጅት ለማድረግ ቅድመ ሁኔታ ያስፈልጋል።

ወጣቶች ምርጫው በኋላ በሚኖረው ውጤት ለፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ከወዲሁ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁማለች።

ከዚህ ቀደም በተካሔዱ ብሄራዊ ምርጫዎች ወጣቶች በታዛቢነት፣በመራጭነትና በማስተማር መሳተፋቸውን አስታውሳ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊነት መንፈስ የነበረው በመሆኑ "ዴሞክራሲያዊ ነው" ማለት እንደማያስደፍር ተናግራለች።

ለዚህም "በምርጫ ወቅት አይተን የታዘብናቸውና ሃሳብ መስጠት ባልቻልንበት ሁኔታ ወጣቶችም ጎራ ለይተው የአንድ ፓርቲ ደጋፊነት  የሚታይበት ነበር" ትላለች።

ያንን አመለካከት ለመስበርና አሁን የተፈጠረውን እድል ለመጠቀም ወጣቶች በነጻነት በመራጭነት፣ አስፈጻሚነትና ተመራጭነት እንዲሳተፉ ግንዛቤ ለማስያዝ ጊዜ ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ አሁን ካለው አመራር ወጣቱ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ እንደሚጠብቅ ገልጻ ጥያቄውን የሚመልስለት ተወካይ በመምረጥና በታዛቢነት በመሳተፍ መብቱን መጠቀም ይኖርበታል።

በአፍሪካ ምርጫዎች ሲካሄዱ ሰላማዊ ቢመስሉም ውጤቱ ይፋ ሲሆን በሚፈጠረው ብጥብጥ ብዙ ጊዜ ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚሆነው ወጣቱ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ብሄራዊ ምርጫም ስሜታዊ ሳይሆን በሰከነ መንፈስ ውጤቱን በሰለጠነ መንገድ እንዲቀበል ግንዛቤ ለመስራት ማቀዳቸውን ተናግራለች።

ወጣት ጽጌሬዳ የወጣቱ ቁጥርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አለመጣጣም ወደ ስደት፣ ሁከትና ብጥብጥ እንዴሄድ አድርጎታል የሚል ሃሳብ አላት።

ጥያቄው ከኢኮኖሚ ችግር አልፎ የፖለቲካ ችግር በመሆኑ ለምርጫ ብዙ መስራት እንደሚጠይቅም ገልጻለች።

በየአምስት ዓመቱ የሚከናወነው ምርጫ በ2012 ዓ.ም በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደሚካሄድ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም