አሉታዊ አመለካከቶችን በማስወገድ ተምሳሌነታችንን በአንድነት እናረጋግጣለን....የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

96

ሐረር ሚያዝያ 6/2011 ለአገር እድገት የማይበጁ አሉታዊ አመለካከቶችን በማስወገድ ተምሳሌነታችንን በአንድነት እናረጋግጣለን ሲሉ በጽዳት ዘመቻ የተሳተፉ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ።

ተማሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትለው ዛሬ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የጽዳት ዘመቻ አካሂደዋል።

ተማሪዎች በእዚህ ወቅት እንዳሉት ለአገር እድገትና ሰላም የማይበጅ አሉታዊ አስተሳሰቦችን እንደ ቆሻሻ በማስወገድ ተምሳሌትነታቸውን በአንድነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራሉ።

በጽዳት ሥራው ከተሳተፉት መካከል በዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት የጋዜጠኝነት ተማሪ ዝናሽ ደሳለኝ እንዳለችው የጽዳት ዘመቻው ሁሉንም ተማሪ ያሳተፈና ቀጣይነት ያለው ሊሆን ይገባል።

"ጽዳት ከሚኖረው የጤና ጥቅም ባለፈ ተጋግዘንና ተባብረን የሚጠቅመንን የምናጠናክርበት እንዲሁም ለተቋሙም ሆነ ለአገር የማይበጅ አስተሳሰብን በጋራ የምናስወግድበት ነው" ብላለች።

"የጽዳት ሥራው ከበሽታ እንድንጠበቅ ከማድረግ ባለፈ ለጋራ ጉዳያችን በአንድነት እንድንነሳና ህብረታችን እንዲጠናከር ይረዳል" ያለው ደግሞ የሁለተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ናወል ክበበው ነው።

ከመንገድ ላይ ቆሻሻን ማጽዳት ብቻ ሳይሆን የሰዎችን አመለካከት መቀየር እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ በተለይ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ያለውን  አሉታዊ አስተሳሰብ በመቀየር አርአያነት ያለው ተግባር ለመፈጸም መዘጋጀቱን ገልጿል።

የጽዳት ዘመቻው አስተባባሪ ተማሪ ኦፍታናን ኃይሉ በበኩሉ " የጽዳት ዘመቻው አካባቢን ከማጽዳት ባለፈ የተዛባ አመለካከትና መከፋፈልን በመተው ሁሉን ወደአንድነት ለማምጣት ያለመ ነው " ብሏል።

ተማሪዎች በጽዳት ዘመቻው የጀመርነውን አንድነት በቀጣይም በተግባር በማሳየት ተምሳሌነታችንን እናረጋግጣለን ሲልም ተማሪ ኦፍናን ተናግሯል።

በዘመቻው ላይ የተገኙት የጸጥታ አስተባባሪው ኢንስፔክተር ወንድመአገኝ መላኩ በበኩላቸው "የጽዳት ዘመቻው ተማሪዎች የማይበጅና የማይጠቅም ተግባራትን በጋራ በማስወገድ ለአንድ ዓላማ እንዲንቀሳቀሱ ያነሳሳል" ብሏል።

"አገር የተገናባው በጋራ ነው፤ የአገር ሰላምና እድገትም የሚጠበቀው ህብረት ሲኖር ነው" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ጉዳይና የአስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጀይላን ወልይ ናቸው።

"ሀገራዊ የአንድነት ስሜት ለመያዝና አላስፈላጊ አመለካከትን ማስወገድ እንደሚቻል ግንዛቤ ለመያዝ ዘመቻው የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

ሁሉም ሰው ሀገሪቱን ወደኋላ ለሚጎትት አሉታዊ አስተሳሰብ ትኩረት መስጠት እንደሌለበት ጠቁመው " በተለይ ሀገርና ህዝብ የሚጎዶ አመለካከቶችን በጋራ መዋጋት ይገባናል" ሲሉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የጽዳት ዘመቻው ዛሬ ጠዋት በሐረር ከተማም የተከናወነ ሲሆን በዘመቻውም የምስራቅ ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የሐረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም