በመዲናዋ በየቀኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የጉዞ ፍላጎቶች አይስተናገዱም

73
አዲስ አበባ ግንቦት 26/2010 በአዲስ አበባ በየቀኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የጉዞ ፍላጎቶች ሳይስተናገዱ ይቀራሉ። ከአስኮ መገናኛ በመመላለስ የሚሰሩት አቶ አክሊል ማናዬ ጠዋት ቀደም ብለው በመነሳት ስራቸው ላይ ቢደርሱም ከስራ ሲመለሱ ግን በፈለጉት ሰዓት ቤታቸው መግባት እንደማይችሉ ይናገራሉ። በትራንስፖርት ችግር ምክንያት አማራጭ በማጣት ለኮንትራት ታክሲ ተጨማሪ ወጪ ማውጣታቸውንም ይገልጻሉ። ከአየር ጤና መገናኛ እየተመላለሰች የምትሰራውና በግል ስራ ላይ የተሰማራችው ዘይባ መሐመድም እንዲሁ በትራንስፖርት ማጣት ምክንያት በስራ ገበታዋ ላይ በሰዓቱ መድረስ እንዳልቻለች ትናገራለች። "በጠዋት ተነስቼ ታክሲ ብጠባበቅም ተጋፍቶ ለመግባት ጉልበት ስለሚጠይቅ ከማርፈዴ በተጨማሪ አልፎ አልፎም ከስራ ቦታዬ የምደርሰው ከሰዓት በኋላ ነው" ትላለች። በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የትራንስፖርት ችግር በርካቶችን ከስራ የሚያስተጓጉልና የሚያማርር ሆኖ ይስተዋላል። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ይህን የቅሬታ ምንጭ የሆነውን የህብረተሰቡን የጉዞ ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አስማረ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ አምስት ሚሊዮን 600 ሺህ የጉዞ ፍላጎቶች ቢኖሩም ማሟላት የተቻለው ሶስት ሚሊዮን የሚሆነውን ነው። በዚህም ምክንያት በየቀኑ ሁለት ሚሊዮን 600 ሺህ የጉዞ ፍላጎቶች ሳይሟሉ ይቀራሉ። የህብረተሰቡን የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር ለመቀነስ ዘርፈ-ብዙ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል የሚሉት ስራ አስኪያጁ 850 የከተማ አውቶቡሶች ተገዝተው አገልግሎት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለተማሪዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ 100 አውቶብሶችና ሌሎች 50 ተደራራቢ አውቶብሶችም አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታውሰዋል። ከመጪው የሐምሌ ወር ጀምሮም 700 ተጨማሪ የከተማ አውቶቡሶች በአዲስ አበባ አገልግሎት እንደሚጀምሩም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል። በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ የጉዞ ፍላጎትና የአቅርቦት መጠን ለማቀራረብ የግል ባለሃብቶች በትራንስፖርት ዘርፍ እንዲሰማሩ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል። 74 በመቶ የሚሆነውን የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ሚኒባስ ታክሲዎች፣ የሀይገር መካከለኛ አውቶቡሶችና ቅጥቅጥ ተብለው የሚጠሩት አውቶቡሶች መሆናቸው ተገልጿል። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን በከተማዋ በአሁኑ ወቅት ያለውን የ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን የጉዞ ፍላጎቶች ለማሟላትና የወደፊቱንም ግምት ውስጥ በማስገባት ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። በመንግስትና በግል ባለሃብቶች በኩል የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረግ ከተፈቀደው በላይ ማስከፈልንና መጫንን ለመሳሰሉ ችግሮች መፍትሄ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም