አካባቢያችንን ስናጸዳ ከጥላቻና ዘረኝነት እሳቤዎች እየነፃን መሆን ይገባል- የፅዳት ተሳታፊዎች

96

አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2011 አካባቢያችንን ስናጸዳ ውስጣችንን ከሚያቆሽሹ የጥላቻና ዘረኝነት እሳቤዎች እራሳችንን እያነፃን መሆን እንደሚገባ ተጠቆመ።

አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ ዛሬ ሲጀመር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጽህፈት ቤታቸው ሰራተኞች ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ጎዳናዎችን አጽድተዋል።

በጽዳት ዘመቻውም ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሰራተኞች በተጨማሪ ታዋቂ ግለሰቦችና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋጋራቸው ግለሰቦች እንዳሉት፤ የአካባቢ ጽዳት ውስጣዊ ማንነትን ከሚያቆሽሽ የአስተሳሰብ ጽዳት ጋር ተሳስሮ መሄድ አለበት።

አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ቆሻሻን 'ከእከሌ ቤት የወጣ ነው' ብለን መርጠን እንደማናጸዳ ሁሉ ሰውን በጎሳ፣ ዘርና ሃይማኖት መርጠን መውደድ አይገባም ብሏል።

ጤናማ አኗኗር የሚሻ ሰው ጤናማ አስተሳሰብ ሊይዝ ይገባልም ነው ያለው።

የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክርታሪ የውጭ ቋንቋዎች ክፍል ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም አካባቢያችንን ለማጽዳት የሚደረግ መሰባሰብ ለአንድ ዓላማ በጋራ የመሰለፍ ባህል አንዲጎለብት ሚናው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከአካባቢ ጽዳት በተጨማሪ ለውስጣዊ የአስተሳሰብ ጽዳት ትኩረት ሊሰጥ ይገባልም ነው ያሉት፤ማንኛውም ግለሰብ ቀስቃሽ ሳይኖረው ለአካባቢው ጽዳት በኃላፊነት አንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

"ከአካባቢያችን በተጨማሪ ጥላቻና መጠላለፍን አጽድተን ለኢትዮጵያ ልማት በጋራ አንቁም" ያሉት ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወይዘሮ ደሚቱ ሃምቤሳ ናቸው።

የጽዳት ዘመቻው ወጤታማ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የሚኖርበትን አካባቢ እንደ ቤቱ ቆጥሮ የማፅዳት ልምድ እንዲኖረውም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም