አካባቢውን ያነቃቃ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኝት

58

ምናሴ ያደሳ-  (ኢዜአ)   የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ ሰሞኑን በኢሉአባቦርና ቡኖ በደሌ ዞኖች ተገኝተው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በልማትና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ካለፉት 27 ዓመታት ወዲህ የሀገሪቱ መሪ በአካባቢው በመገኘት ከሀዝቡ ጋር በቅርበት ሲወያይ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ከነዋሪዎች የተሰጠ አስተያየት አመላክቷል።

የመቱ ከተማ ነዋሪ አቶ አሰፋ አጋ  እንዳሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካባቢያችው መገኘት መንግስት የህዝቡን ችግር በመረዳት መፍትሄ ለመሰጠት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

"ለረጅም ጊዜ ስናነሳችው የነበሩ በርካታ ችግሮች አሉብን፤ ጥያቄዎቻችን  በአጭር ጊዜ መልስ ባያገኙ እንኳ  መንግስት ሊያዳምጣችው ወደ አካባቢያቸው መምጣቱ  ያስደስተናል" ብለዋል ።

አካባቢው እንደ ቡናና ቅመማ ቅመም ያሉ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች በስፋት የሚመረቱበት ቢሆንም የአካባቢው ልማት በመንግስት ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ ሲፈጥር መቆየቱን አስታውሰዋል ።

"ጠቅላይ ሚንስትሩ መጥተው ስለችግሮቻችን ከኛ ጋር መወያየታችው ትልቅ መነቃቃት ፈጥሮልናል"ብለዋል አቶ አሰፋ ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድና የከልሉ ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ መቱ ከተማ ሲገቡ በርካታ ቁጥር ያለው የከተማው ነዋሪና የመቱ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሬዝዳንቱ  በከተማው በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመቱ ከተማ ለሚያስገነባው ዘመናዊ የግብይት ማዕከል የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በኢሉአባቦር ዞን ማረሚያ ቤት በህግ ታራሚዎችና በማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች የተገነባውን  አረንጓዴ የመዝናኛ ስፍራንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ከተወጣጡ የተለያዩ የሀብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማትና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ከ3ሺህ 200 ካሬ ሜትር በላይ ቦታ ላይ የሚገነባው ይህ ዘመናዊ የግብይት ማዕከል ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘው ነገራ ተናግረዋል።

"ለግንባታው የዲዛይን ስራ ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት የተቋራጭ መረጣ ስራ እየተከናወነ ነው" ብለዋል ።

በኢሉአባቦር ዞን  172ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት በቡና መልማቱና በየዓመቱም 80ሺህ ቶን የሚሆን ምርት መሰብሰቡ ለግብይት ማዕከሉ ግንባታ እንዲጀመር ምክንያት መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል ።

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ የማእከሉ መገንባት በአካባቢው ለሚመረቱ የወጭ ምርቶች መጠን መጨመርና ጥራት መጠበቅ አስተዋፆ የጎላ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጎበኘው የከተማው አረንጋዴ የመዝናኛ ስፍራው ያለ መንግስት በጀት በማረሚያ ቤቱ የህግ ታራሚዎችና ሰራተኞች የሙያ፣ የዕውቀትና የጉልበት ተሳትፎ የተገነባ ነው።

የህግ ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አነሳሸነት የተለያዩ የዛፍ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሳር ዝርያዎችን በመትከልና በአካባቢው የነበረውን ወንዝ ከአረም ነጻ በማድረግ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ፍጥረዋል።

የተለያዩ የማረፊያ ቤቶችና የመዋኛ ገንዳዎችም የሙያው ባለቤት በሆኑ የህግ ታራሚዎች አማካኝነት በመዝናኛ ማዕከሉ ተገንብተዋል።

በአካባቢው ጥንታዊ የገዳ ስርዓት (ሰግለን ኢሉ) አምሳያ የተገነቡ ዘጠኝ ባህላዊ ቤቶችን ደግሞ በማዕከሉ ማራኪ የቱሪዝም ስፍራ ፈጥረዋል።

አረንጓዴና ተፈጥሮዊ  ማዕከሉ ለከተማውና አካባቢው  ማህበረሰብ  መዝናኝ ስፍራ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝናኛ ስፍራውን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን በኢሉ አባቦር ዞን ማረሚያ ቤቶች ኃላፊ ኮማንደር ተናኜ ወልዱ ገለጻና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሬዝዳንቱ  በመቱ ከተማ ቆይታቸው ከኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች ጋር  በተወያዩበት ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

የሰግለን ኢሉ አባ ገዳ ከሊፋ ሾኖ እንዳሉት ለያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ተብሎ ከአካባቢያቸው የተነሱ አርሶአደሮች ከቦታቸው ሲፈናቀሉ በቂ ካሳ ባለማግኘታቸው ለጉዳት ተጋልጠዋል።

ግንባታው ከተጀመረ ከአስር ዓመታት  በላይ ቢቆጠርም  የአካባቢው ተወላጆች በስራ ዕድል ተጠቃሚ ባለመሆናቸው በአካባቢው ለሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል ።

የፋብሪካው ግንባታ መጓተት  ለአካባቢውና ለሀገር ልማት የሚጠበቅበትን እንዳይወጣ በማድረጉ መንግስት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠው  ጠይቀዋል።

በመቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሸምሱ ሁሴን በበኩላቸው ቀበሌያቸው በመቱ ወረዳ ስር የሚተዳደር መሆኑን ተናግረዋል ።

"ቀበሌው ሰፊና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዘ በመሆኑ መንግስት በወረዳ ደረጃ ሊያዋቅረው ይገባል" ሲሉ አንስተዋል።

በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች በተለያዩ አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሀ ተቋም ባለመኖሩ መቸገራቸውን የገለፁት ነዋሪዎቹ መንግስት ችግሩን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል ።

በሀገሪቱ ከጢስ አባይ ቀጥሎ በትልቅነቱ ሁለተኛው የሆነውና በመቱና በቾ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኘው  የሶር ወንዝ ፏፏቴና በዩኒስኮ የተመዘገበው የተፈጥሮ ደን  መዳረሻ የመንገድ መሰረተ ልማት ተማልቶላቸው ለቱሪዝም ልማት እንዲውሉ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ነዋሪዎቹ አንስተዋል።

የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም በህዝብ መካከል ግጭት ለመፍጥርና ሀገር ለመበጥበጥ የሀሰት መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ  አካላት መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል ።

በተለያዩ አካባቢዎች በህገወጥ እንቅስቃሴ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ለመውስድ መንግስት ከተገቢው በላይ ትዕግስት አሳይቷል፤ ለምን የሚሉትም  በነዋሪዎቹ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይና የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ  ከነዋሪዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ መንግስት በሁሉም መስኮች የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

"በተለያዩ ችግሮች የተጓተተው የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ  ግንባታን የውጭ አካላትን ጭምር በማሳተፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መንግስት ትኩረት ስጥቶ እየሰራ ነው " ብለዋል ።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ሀገሪቱንና ህዝቧን ለመጉዳት የሚደረጉ ኃላፊነት የጎደላችው እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ህግ እያወጣ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለያየ መልኩ የሚደርጉ ህገ-ወጥ እንቅሰቃሴዎችን ለመቆጣጠር መንግስት ጥፋተኞችን ከማሰር ይልቅ በትዕግስት፣ በመውያየትና በመመካከር ከጥፋት እንዲመለሱ የሚያስችል አማራጭ እየተከተለ መሆኑን አብራርተዋል ።

መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመመለስ አንድነቷና ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ለመገንባት እያደረገ ላለው ጥረት ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር ከጎኑ እንዲቆም ጠቅላይ ሚኒስተሩ ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ "በዞኑ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆነው የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የዘገየው በቦታ መረጣ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች በመነሳታችው ነው" ብለዋል ።

ግንባታውን በፍጥነት ለመጀመር መንግስት ቁርጠኝ  መሆኑን አረጋግጠዋል ።

የንጹህ መጠጥ ውሀ ችግር በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ የክልሉ መንግስት አንደ ችግሩ ግዝፈትና ቅደም ተከተል ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ከፍተኛ የውሀ ችግር ላለባቸው ቆላማና አርብቶ አደር  አካባቢዎች  ቅደሚያ የመስጠት ካልሆነ በስተቀር የአካባቢውን የውሀ ችግር ለመፍታት መንግስት ትኩረት ሳይሰጥ አለመቅረቱን ገልፀዋል ።

የወረዳ መዋቅር ጥያቄ በተመለከተ መንግስት በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ በመሰጠት  ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ ለማ ራሱን ችሎ የተዋቀረውን የቡኖ በዴሌ ዞን በአብነት አንስተዋል።

"ሆኖም ከመንገድ መርዘምና ተያያዥ ችግሮች ጋር ለሚነሳው የመዋቅር ጥያቄ ዋነኛው መፍትሄ የመሰረተ ልማት ማዳረስ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል" ብለዋል አቶ ለማ መገርሳ ።

"ወረዳዎችንና ቀበሌዎችን በመከፋፈል ለመንግስት መስሪያ ቤቶች መገልገያ ቁሳቁስ ወጪና ለስራ ማስኬጃ በጀት ሀብት ከማባከን ለተለያዩ የመሰረት ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት መሰጫ ተቋማት ግንባታ ማዋል ይበልጥ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል " ሲሉም ተናግረዋል ።

ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ራሱንና ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

በህዝቡ መካከል መደማመጥና አንድነትን በማጎልበት ሀገራዊ ለውጡ ስኬታማ  እንዲሆን የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች የበኩላቸውን እንዲወጡም አቶ ለማ  ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም