ክልሎቹን በልማት በማስተሳሰር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሰራን ነው - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

85

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2011 የቤንሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎችን በልማት በማስተሳሰር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ሰላም መስፈኑን አስታውቀዋል።

መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም የካማሼ ዞን አመራሮች ከምዕራብ ኦሮሚያ አስተዳደር ጥምር ኮሚቴ ጋር የነበራቸውን ስብሰባ አጠናቀው እየተመለሱ በነበሩ የዞን፣ የወረዳ አመራሮችና የፀጥታ ኃይሎች ላይ በተከፈተው ተኩስ የ4 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ስፍራዎች በተከሰተ ግጭት ህይወት አልፏል። በርካታ ዜጎችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

አቶ አሻድሊ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ለረጅም ዘመናት አብረው በኖሩ ህዝቦች መካከል ቅሬታ ተነስቷል።

ይህን ችግር ለመፍታት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የጋራ የሰላም ኮንፈረንስ ከማድረግ ጀምሮ ክልሎቹ በልማት እንዲተሳሰሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

''ክልሎቹን በልማት በማስተሳሰር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሰራን ነው'' ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ በአሁን ጊዜም በክልሉ ሰላም መስፈኑን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አሻድሊ ገለጻ፤ በክልሉ ያለውን የወጣቶች ስራ አጥነት ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት በከተማና በገጠር የተሻለ ውጤት እየመጣ ነው።

በቀጣይም የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ተዛማጅ ችግሮችን መፍታትና የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን ማመቻቸት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 50 ሺህ 380 ስኩየር ኪሎ ሜትር ሲሆን ደጋ፣ ቆላና ወይና ደጋ የአየር ንብረት ባላቸው ሦስት ዞኖች፣ 19  ወረዳዎች፣ አንድ ልዩ ወረዳ እና በአንድ የከተማ አስተዳደር የተዋቀረ ነው።

የክልሉ ነባር ብሔረሰቦች ተብለው ከሚታወቁት አምስት ብሔረሰቦች (በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ) በተጨማሪም የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአገው፣ የትግሬ፣ የሃድያ እና የሌሎች ብሔረሰቦች በብዛት ይገኙበታል። የብሔር፣ ብሔረሰቦቹ ቋንቋዎች በስፋት የሚነገሩ ሲሆን፤ አማርኛ የክልሉ የሥራ ቋንቋ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም