ሁለተኛው አገር አቀፍ የባህልና ጥበብ አውደጥናት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

110
ወልዲያ ግንቦት 26/2010 ሁለተኛው አገር አቀፍ የባህልና ጥበብ አውደጥናት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ትናንት ተካሄደ፡፡ “ኢትዮጵያዊ ባህልና ጥበብ ለኢትዮጵያዊነት “በሚል ርእስ በተካሄደው በዚሁ አገር አቀፍ አውደጥናት ላይ ከስምንት ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ 400 ያህል ምሁራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባየ ይማም በአውደ ጥናቱ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ እንደገለፁት ወጣቱ ባህላዊ እሴቶቹን በሚገባ ተገንዝቦ ተግባራዊ እንዲያደርግ ከቤተሰብ ጀምሮ ሊሰራ ይገባል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ለዘመናት የዘለቀው የመቻቻልና አብሮ የመኖር እንዲሁም የመረዳዳት እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ፣ የትምህርት ተቋማትና ባህልና ቱሪዝም አስፈላጊውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የፍልስፍና ምሁሩና ተመራማሪው ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስወገድ አኩሪ ባህሉን ጠብቆ ለማቆየት ሊተጋ እንደሚገባ  አሳስበዋል፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያው አቶ ሰርጸ ፍሬስብሐት ‘’ከሥነ ጥበባት ህብራዊ ባህርይ ምን እንማራለን ‘’ በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሑፍ ''ዜማ፣ ግጥምና የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች አንድነትና ህብር ፈጥረው ውብ ኦርኬስትራ እንደሚያስገኙ ሁሉ የተለያዩ ባህሎችም ህብር ሲፈጥሩ አገራዊ አንድነት ያመጣሉ'' ብለዋል፡፡ በወልድያ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ክፍል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት መለሰ  በበኩላቸው ኢትዮጵያዊ ባህልን ለትውልዱ ማስረጽ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑ የአውደ ጥናቱ መሪ አሳብ ‘’ኢትዮጵያዊ ባህልና ጥበብ ለኢትዮጵያዊነት’’ የሚል ርእስ መመረጡን ተናግረዋል፡፡ በወልድያ ዩኒቨርስቲ የባህልና ሥነ ጽሑፍ ማእከል በተዘጋጀው በዚሁ አገራዊ ዐውደ ጥናት የግእዝ ድርሳናት ለዘመናዊ ትምህርት ልማት ያላቸው አስተዋጽኦና የቋንቋ ፖሊሲና አተገባበር በኢትዮጵያ በሚሉ ርእሶች ላይም አጫጭር ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም