የዘረ መል (ዲ ኤን ኤ) ምርመራ በአገር ውሰጥ ሊጀመር ነው

362
አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2010 የግለሰቦችን ማንነት ጨምሮ ልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያትን የሚጠቁመውን ዘረ-መል (ዲ ኤን ኤ) ለማወቅ የሚያስችለውን ምርመራ በሚቀጥለው ዓመት በአገር ውስጥ ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ። የዘረ-መል ምርመራ በተለይም ወንጀሎችና አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት የሰዎችን ማንነትና ሌሎች ተያያዥና ወሳኝ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ ነው። የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ባለሙያዎችና የተለያዩ የፍትህ አካላት ተወካዮች ዛሬ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ምርመራ ማእከል የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል። የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ፍቅሬ ወልደ ገብርኤል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የዘረ-መል (ዲ ኤን ኤ) ምርመራ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ አይሰጥም፤ በመሆኑም አገልግሎቱ የሚገኘው ለአንድ የዘረ መል ምርመራ አስከ 80 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ በተለያዩ የውጭ አገራት ነው። የምርመራ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል አቅም በአገር ውስጥ መፈጠሩም ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በቅርበትና በፍጥነት እንዲያገኝ ከማድረግ በተጨማሪ ለአገልግሎቱ የሚያወጣውን ከፍተኛ ወጪ ያስቀራል ብለዋል። አገልግሎቱን ለመጀመር እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ያላቸው ሙያተኞች የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ስልጠናዎች እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን ጥናትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መከናወናቸውንም ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል። ኮማንደር ፍቅሬ አክለውም በመጪዎቹ ጊዜያት የመሳሪያዎች ግዢ የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰው የምርመራ አገልግሎቱን በመጪው ዓመት ለመጀመር መታቀዱን አመልክተዋል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በመርዛማ ኬሚካሎች የሚፈጸሙ ወንጀሎች (ፎረንሲክ ቶክሶሎጂ) ምርመራ አገልግሎትን የሚጠይቁ አካላት ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ማዕከሉ ይህንኑ አገልግሎት በአገር ውስጥ ለመስጠት ባለሙያዎችን በዘርፉ እንዲሰለጥኑ በማድረግ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል። ዳይሬክተሩ አንዳሉት ማዕከሉ የሰነዶች፣ የአሻራ፣ የቃጠሎ፣ የጦር መሳሪያዎች፣ የፍንዳታ፣ የአደገኛ ዕጾችና የሳይበር ወንጀሎች ምርመራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እየሰጠ ነው። ሆኖም በበጀት እጥረት ሳቢያ በየጊዜው እየተሻሻሉ የሚሄዱ "ሶፍትዌሮች ግዢ መፈጸም ባለመቻሉ የተወሰኑ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ታግዞ መስጠት አልተቻለም" ብለዋል። የፎረንሲክ ዘርፍ ስልጠና በውጭ አገራት ብቻ የሚሰጥና ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ መሆኑና የባለሙያዎች ደመዋዝና ጥቅማ ጥቅም ማነስ ማእከሉ ካሉበት ችግሮች መካከል መሆናቸውን ኮማንደር ፍቅሬ አስረድተዋል። ከዚህም ሌላ ለቤተ ሙከራ ምርመራዎች ምቹ ክፍሎችና አደረጃጀቶች አለመኖራቸውም ሌሎች ማእከሉን እየገጠሙት ያሉት ችግሮች ናቸው ብለዋል። ያም ሆኖ ከቦታ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታት በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ በጀትና ቦታ የማዘጋጀት ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው የባለሙያዎች ደሞውዝና ሌሎች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ላይም መንግስት ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም