አክሱምን ከጎበኙ ቱሪስቶች 135 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተገኘ

94

አክሱም ሚያዚያ5/2011 በአክሱም ከተማና አካባቢው የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ከጎበኙ ቱሪስቶች   135 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተገኘ።

የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት  ምክትል ኃላፊ አቶ ተክላይ ገብረመድህን ለኢዜአ እንደተናገሩት ገቢው የተገኘው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በስፍራው የሚገኙ ታሪካዊ፣ጥንታዊና ተፈጥሯዊ  መስህቦች  ከጎበኙ 50 ሺህ ያህል የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ነው።

ከቱሪስቶች መካከልም 20 ሺህ ያህሉ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የመጡ ናቸው፡፡

ስፍራውን  የጎበኙት  የውጭና የሀገር ውስጥ  ቱሪስቶች   ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ18 ሺህ ብልጫ እንዳለው  አቶ ተክላይ ገልጸዋል፡፡

የቱሪስቶችን ቁጥር መጨመር ተከትሎ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአገልግሎትና ከመግቢያ ትኬት ሽያጭ  134 ሚሊዮን 955 ሺህ ብር ገቢ ተገኝቷል።

የጎብኚዎች  ቁጥር ሊጨምር የቻለው የቱሪስት ቦታዎችን ለማስተዋወቅ በተደረገው ጥረትና   በትግራይ ክልል ባለው አንጻራዊ ሰላም መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የውጭ  ጎብኝዎች  የአንድ ቀን አማካይ ቆይታ ወደ ሦስት ቀናት ማሳደግ ተችሏል፡፡

በአክሱም ከተማ በአስጎብኝነት ስራ የተሰማሩት አቶ ኤፍሬም ብርሃነ በተያዘው ዓመት  የቱሪስቶች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ቱሪስቶችን ለማስጎብኘት አንድ ተሽከርካሪ ብቻ እንደነበራቸውና ገቢያቸው በማደጉ ሌላ ተጨማሪ  በ800 ሺህ ብር መግዛታቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ስራ  የተሰማራው ወጣት እዝግንአምን በርህ እንዳለው  በሚሰጠው አገልግሎት ጥሩ ገቢ እያገኘ ነው፡፡

ስራውን ለማስፋት እንዲያግዘው  ተሽከርካሪ ለመግዛት ማቀዱን አመልክቷል።

ለቱሪስቶች ባህላዊ አልባሳትን በመሸጥ የምትተዳደረው የአክሱም ከተማ ነዋሪ  ወጣት የኔትሁን ሳዲቅ በበኩሏ  የቱሪስቶች ቁጥር መጨመር ጥሩ የገበያ እድል እንደተፈጠረላት ተናግራለች። በዘርፉ ለ540 ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም