የአዋቂዎች እንቢተኝነትና የተግባቦት ክፍተት በኢትዮጵያ የስርዓትና የተቋማት ግንባታ ተግዳሮት ሆነዋል…ምሁራን

158

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2011 የአዋቂዎች እንቢተኝነትና የተግባቦት ክፍተት በኢትዮጵያ የስርዓትና የተቋማት ግንባታ ላይ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ምሁራንና ተመራማሪዎች ገለጹ። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት "አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ስርዓትና ተቋማት ምንድን ናቸው፣ የስርዓትና የተቋማት ግንባታ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ዳራ ምን ይመስላል፣ የአመለካከትና የስነ ምግባር ቁመናችን ከስርዓትና ተቋማት ግንባታ አንጻር ምን ይመስላል፣ ለማበልጸግ ምን ይጠበቅብናል፣ እንዲሁም ስርዓትና ተቋማትን ማጠናከር በተመለከተ አዲሱ መንግስት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ምን እርምጃ ወሰደ ምን ይቀረናል በሚል ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል። 

የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው፣ የአቅም ግንባታና የአመራር ልማት ባለሙያ ወይዘሮ ህይወት አለማየሁ እና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየሱስ የውይይት ሀሳብ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በመድረኩ ላይ ባቀረቡት የውይይት ሀሳብ  በኢትዮጵያ የስርዓትና የተቋማት ግንባታ ላይ የባህልና የአመለካከት ችግሮች አሉ። 

ለውጥና አዲስ ነገርን ለመቀበል የስነ ልቦና እንቢተኝነት እንዳለ የገለጹት ፕሮፌሰር ዳንኤል የማህበራዊ ተግዳሮቶችና ጽንፈኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ አስረድተዋል። 

እንደ ፕሮፌሰር ዳንኤል ገለጻ በኢትዮጵያ የስርዓትና የተቋማት ግንባታ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች ለማስወገድ የልቦና ውቅር ንቅናቄ ማድረግ ያስፈልጋል። 

በዓለም ላይ በርካታ ለውጦች በሚታዩበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ለመቀየር ዝግጁ መሆንና የሚገጥማቸውን ነገር በቀጥታ ማየት እንዳለባቸው አስረድተዋል። 

የመምህራንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መለወጥ የመጀመሪያ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ያስረዱት ፕሮፌሰር ዳንኤል በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን መለወጥ በአገር አቀፍ የለውጥ ሐዋርያ ሆነው ሊሰሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል። 

ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ የወጡ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ያወጣቸው አካል ራሱ የማክበርና የማስከበር ችግር እንዳለ ገልጸዋል።  

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የወጡ ህጎችን ያወጣው አካል ተዓማኒነትና ህጎች ማክበር ላይ ተግዳሮቶች እንዳሉ አብራርተዋል። 

የአቅም ግንባታና የአመራር ልማት ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ህይወት አለማየሁ በበኩላቸው ተቋማት ህያው ሆነው በጥሩ ቁመና ላይ ሲገኙና ጠንካራ ሲሆኑ የመንግስትን ቅርጽ እስከመቀየር ድረስ አቅም እንዳላቸው አብራርተዋል። 

''በአሁኑ ወቅት ስለ ተቋማት ግንባታ ለማወራት፣ የመጣውን ለወጥ ወደ ታች ለማውረድ እንዲሁም በማህበራዊ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በተረጋጋ መንገድ በለውጥ ስርዓት ውስጥ መጓዝ ያስፈልጋል'' ብለዋል።  

በአሁኑ ወቅት በተቋማት ውስጥ በርካታ ችግሮች ያሉ ሲሆን በተለይ ተልዕኮን መወጣትና ራዕይን ማሳካት ላይ ሰፊ ተግዳሮቶች እንዳሉ ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ ያሉ ተቋማት የራስ ስለሆኑና ቅቡል ሆነው ስለመጡ የማስተካከልና የመገንባት አቅም እንዳለ የገለጹት ወይዘሮ ህይወት በፖለቲካ የመጣውን ለውጥ በሲቪል ሰርቪሱም ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል። 

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየሱስ በበኩላቸው ባለፉት አስራ ሁለት ወራት መንግስት የስርዓትና የተቋማት ግንባታ ጉዳዮችን በደንብ በትኖ የማየት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ መዳከም፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ ሌብነት፣ የዜጎች የኑሮ ደረጃ ማሽቆልቆል የፈጠረው ህዝባዊ ብሶት ከግምት ውስጥ ገብቶ መሰራቱን አስረድተዋል። 

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን የሚያሳልጡ ስርዓቶችና ተቋማት እንደተለዩ የገለጹት አቶ በዛብህ ተለያይተው የነበሩትን መልሶ የማገናኘት እንዲሁም ድርብ ኃላፊነት የተሸከሙ ተቋማትን የመለየት ስራ መሰራቱን አብራርተዋል። 

በቀጣይ በስርዓትና በተቋማት ግንባታ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ የሚያጋጥም ተግዳሮት እንደሆነም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም