በአፋር የህግ የበላይነትና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ መብት ለማረጋጋጥ እየተሰራ ነው...የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ

55

ሰመራ ሚያዝያ 4/2011 ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎየህግ የበላይነትና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ መብት ለማረጋጋጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የአፋር ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ ፋጡማ መሀመድ እንዳሉት ሕብረተሰቡ በፍትህ አካላትና ስርአቱ ላይ ያለውን እምነት ለመለስ እየተሰራ ነው።

ለእዚህም የፍትህ ተቋማት አደረጃጀት ከአስፈጻሚ አላካት ወጥቶ ገለልተኛ ሁኖ እንዲደራጅ የሚያስችል የህግ ማዕቅፍና የአደረጃጀት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

"በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ 5 ማረሚያ ቤቶች ምልክታ በማድረግ የህግ ታራሚዎች ያነሷቸው የመኝታና የምግብ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን በመፍታት የማስተካከል ሥራ ተሰርቷል" ብለዋል።

የይቅርታና መደመር ፍልስፍናን ታሳቢ በማድረግም በአምስት ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ለነበሩ የተለያዩ ታራሚዎች ይቅርታ መሰጠቱን አመልክተዋል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁለት ዙር 203 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ነው ወይዘሮ ፋጡማ የገለጹት።

ከእዚህ በተጨማሪ 17 የፌዴራል ህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ለሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት ፋይላቸው መላኩን ጠቁመዋል።

ወይዘሮ ፋጡማ እንዳሉት ከተፈቱት የህግ ታራሚዎች መካከል በቀላል የአካል ማጉደል፣ በስርቆት እንዲሁም በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና በህገወጥ ንግድ ወንጀሎች ተከሰው የተፈረደባቸው ይገኙበታል።

በተለይም በ3ኛው ሩብ ዓመት የተካሄደው ይቅርታ አሰጣጥ በእስካሁኑ የይቅርታ አሰጣጥ ሂደት ከግልጽነትና ከፍትሃዊነት ጋር ይነሳ የነበረውን ቅሬታ የፈታ መሆኑን ተናግረዋል።

ለእዚህም ታራሚዎች በይቅርታ ደንቡ ላይ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ተጠቃሚ እንደሆኑ ስልጠና በመስጠት ግንዛቤያቸውን በማሳደግ ጭምር የተካሄደ መሆኑን በማሳያነት ገልጸዋል።

በይቅርታ ከተፈቱት የህግ ታራሚዎች መካከል ከአውሲረሱ ማረሚያ ቤት ከአንድ ወር በፊት የተፈታው አቶ መሃመድ ጀማል "በማረሚያ ቤት ቆይታዬ ህግ አክብሮ መንቀሳቀስ ያለውን ጥቅም ተገንዝቤያለሁ" ብሏል።

የክልሉ መንግስት በሰጠው የይቅርታ እድል ተጠቅሞ ቀሪ ሕይወቱን ሰላማዊና ስኬታማ ለማድረግ በአካባቢው ልማትና የሰላም እሴት ግንባታ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንደሚሆን ተናግሯል።

ከማረሚያ ቤቱ ከአንድ ወር በፊት በይቅርታ እንደተፈታ የገለጸው አቶ ኡስማን ሙሳ በበኩሉ "በማረሚያ ቤት ቆይታዬ በህግ ላይ ግንዛቤዬን ከማሳደግ ባለፈ የሙያ ስልጠና አግኝቺያለሁ" ብሏል።

በቀጣይ ለሀገርና ለወገን በጎ ተግባር በመፈጸምና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም