የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ ማስፈጸሚያ የስነ ስርዓት ደንብ ላይ እየተወያዩ ነው

104

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2011 የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነዱን ለማስፈጸም በወጣ  የስነ ስርዓት ደንብ ላይ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ላይም የጋራ ምክር ቤቱ  መደበኛ ስብሰባውን  "በዓመት አራት ጊዜ  ያደረጋል" በሚለው ላይ ሰፋ ያለ ሃሳብ አንስተዋል።

በዚህም መጪው የምርጫ ወቅት በመሆኑ "በዓመት አራት ጊዜ ይከናወናል" የተባለው 'መደበኛ ስብሰባ በየወሩ እንዲደረግ' የሚል አማራጭ ሀሳብ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በሰጡት አስተያየት፤ ደንቡ ላይ ማሻሻያ ሲደረግ ሃሳቡ እንደ ግብዓት እንደሚጠቅም አውሰተው፤ የምርጫ ጊዜው በሚቃረብበት ወቅት መደበኛ ስብሰባው በየወሩ ሊካሄድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በተጨማሪም  "ምክር ቤቱ በራሱ ተወያይቶ መፍታት የማይችላቸው ጉዳዮች ሲገጥሙት ምን ያደረጋል? ለፓርቲዎች ፈቃድ መስጠት ለምን ይዘገያል? የፓርቲዎች መመሪያና ደንብ እያልን በየጊዜው በመሰብሰብ  ጊዜያችንን  ማጥፋት የለብንም " የሚሉና ሌሎች ሃሳቦችም ተንሸራሽረዋል።

የቃል ኪዳን ሰነዱ መጋቢት 5 ቀን 2011 የጸደቀ  መሆኑ ይታወቃል ።

የቃል ኪዳን ሰነዱን የፈረሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቋቋሙት የጋራ  ምክር ቤት የሚያስፈፅማቸውና የሚያከናውናቸው ተግባራትና ኃላፊነት በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን፤ የቃል ኪዳን ሰነዱ ፈራሚዎች በግልፅነት በሰነዱ ላይ የተዘረዘሩ አገራዊ ሃላፊነቶችን የሚያከናውኑበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የስነ ስረዓት ደንቡ እንደሚያስችል ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም