በፓርኩ የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ 400 ሄክታር የሚጠጋ የጓሳ ሳር ላይ ጉዳት አደረሰ

143

ጎንደር ሚያዝያ 3/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ዳግም የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ 400 ሄክታር የሚጠጋ የጓሳ ሳር ላይ ጉዳት ማድረሱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ታደሰ ይግዛው ለኢዜአ  እንደገለጹት  ጉዳቱ የደረሰው ግጭ በተባለው የፓርኩ አካባቢ እንደሆነና በዚህ ስፍራ  የእሳት ቃጠሎውን ዛሬ መቆጣጠር ተችሏል፡፡

"ወደ ፓርኩ ገደላማ ስፍራ የተሻገረው የእሳት ቃጠሎ ቢቀንስም ከቦታው አስቸጋሪነት አንጻር መቆጣጠር አልተቻለም " ያሉት አቶ ታደሰ የህብረተሰቡ ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

እሳቱ የተቀሰቀሰበት የግጭ አካባቢ በአብዛኛው የቀይ ቀበሮዎች መኖሪያ እንደሆነ ጠቁመው ቃጠሎው ጉዳት ሳያደርስባቸው ወደ ፓርኩ ሌላኛው ክፍል መሰደዳቸውን አስረድተዋል፡፡

" በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የእሳት ቃጠሎ ምክንያት እስካሁን በውል አልታወቅም" ብለዋል፡፡

ከክልል ፣ከዞንና ከወረዳ የተውጣጣ ግብረ ኃይል የእሳት አደጋውን መንስኤ እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ቃጠሎው በቁጥጥር ስር በዋለበት የግጭ አካባቢ ዳግም ቢነሳ በቅርብ ርቀት መቆጣጠር እንዲቻል ከፀጥታ ኃይሉና ከህብረተሰቡ የተውጣጣ ሃይል በአካባቢው በጊዜያዊነት ዝግጁ ሆኖ እንዲቆይ ተደርጓል "ብለዋል፡፡

በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ ፣ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የበርካታ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም