የጌዴኦ ተፈናቃዮች ለደህንነታችን ዋስትና የምናገኝ ከሆነ ወደ ቀያችን እንመለስ እያሉ ነው

44

ጌዴኦ ሚያዚያ 3/2011 በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች “ለደህንነታችን ዋስትና ከተሰጠን ወደ ቀያችን ለመመለስ ዛሬ ነገ አንልም” እያሉ ነው።

በኦሮሚያ ክልል የምእራብ ጉጂ ዞንና ወረዳ አመራሮች በበኩላቸው “ወደ ቀያቸው መመለስ ለሚፈልጉ የጌዴኦ ተወላጅ ወገኖቻችን የሰላም እጦት ስጋት ሊገባቸው አይገባም፤ መልሰው እንዲቋቋሙም እንደግፋቸዋለን” ብለዋል።

ከምስራቅና ምእራብ ጊጂ ዞን ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ የጌዴኦ ተወላጆች ገደብ ወረዳን ጨምሮ በ17 የተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ሰፍረው ይገኛሉ።

የኢዜአ ሪፖርተር ወደ ስፍራው በማቅናት በተወሰኑት መጠለያ ጣቢያዎች በመገኘት ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዳንዶቹን አነጋግሯል።

ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉትም ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ ህይወታቸውን አደጋ ላይ የጣለ አስገዳጅ ሁኔታ ገጥሟቸው ሲሆን እስካሁንም መመለስ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

በዚህ ምክንያት ለአንድ ዓመት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ኑሯቸውን እየገፉ ያሉት የጌዴኦ ተፈናቃዮች አሁንም ለደህንነታቸው ዋስትና የሚሰጣቸው አካል ካለ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንደማያመነቱ ገልጸዋል።

በገደብ ወረዳ ጎቲቲ ቀበሌ ካሉት 11 መጠለያ ጣቢያዎች መካከል በአንደኛው ያገኘነው ወጣት ኤሊያስ መኩሪያ እንደሚለው እርሱን ጨምሮ በርካቶች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ሞክረው አልተሳካላቸውም።

የአምስት ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ ፍሬነሽ ፀጋም ከጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ሰሬሰባ ቀበሌ ተፈናቅላ ጎቲቲ መጠለያ ጣቢያ መኖር ከጀመረች አንድ ዓመት ሞልቷታል።

ከቀርጫ ወረዳ ቢሊዳኩዙዋ 01 ቀበሌ ተፈናቅለው ጎቲቲ የሰፈሩት አቶ ካሱ መንገሻም ወደ ቀያችን መመለስ ብንሻም እንዴት አድርገን ይላሉ? 

ከቀርጫ ወረዳ ፈልሰው ገደብ መጠለያ ጣቢያ የሰፈሩት አቶ ንጋቱ ጅሶም ወደ ቀያቸው ተመልሰው ድጋሚ ችግር ገጥሟቸው መፈናቀላቸውን ያስረዳሉ።

የጉጂና የጌዴኦ ህዝቦች ተመሳሳይ ባህል አኗኗርና ልምድ ያለን ቤተሰቦች ነን የሚሉት ተፈናቃዮቹ ዳግም ለመገናኘት በናፍቆት እየተጠባበቁ መሆኑንም አልደበቁም።

የምእራብ ጉጂ ዞን አስተዳደር አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው የጉጂና ጌዴኦ ህዝቦች የጋራ እሴት ያላቸው አንድ ህዝቦች በመሆናቸው ተጣልተው እንደማያውቁና ወደፊትም እንደማይለያዩ ያምናሉ።

ሆኖም ከግጭት ትርፍ እናገኛለን ብለው በግልና በቡድን የሚንቀሳቀሱ አካላት ለመነጠል እየሞከሩ በመሆኑ ከጉጂ የተፈናቀሉ ሁሉም የጌዴኦ ተወላጆች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ግጭት በሌለበት የደህንንት ስጋት አይግባቸው ያሉት አቶ አበራ መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አረጋግጠዋል።

በዞኑ የቀርጫ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አበበ ቡቀቶ ተፈናቅለው ከነበሩ የጌዴኦ ተወላጆች ካለፈው መስከረም ጀምሮ ወደ ቀያቸው የተመለሱ እንዳሉ ጠቅሰው ቀሪዎችም እንዲመለሱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አስተዳደራቸውና ህዝባቸው ወገኖቹን በመቀበል ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በገደብ ወረዳ ጎቲቲ ጊዜያዊ መጠለያ ኢዜአ ተዘዋውሮ በተመለከታቸው ጣቢያዎች በወቅቱ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመጡ 24 ዶክተሮችና ነርሶች ህክምና ሲሰጡ አይተናል።

በጎቲቲ በመንግስት የውሃ አቅርቦት እንዲሁም በገደብ መጠለያ ጣቢያ ፒፕል ኢን ኒድ በተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት የንፅህና መጠበቂያና አልባሳት ድጋፍ ሲደረግም አስተውለናል።

በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ ብቻ በ17 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች 344 ሺህ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ከወረዳ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም