አገር አቀፍ የእንቦጭ አረም መከላከያ ስትራቴጂ መነደፉ ተገለፀ

48

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2011 አገር አቀፍ የእንቦጭ አረም መከላከያ ስትራቴጂ መነደፉን የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር አዳነች ያሬድ አስታወቁ።

ባለስልጣኑ የአብያታ ሃይቅ ውሃ መጠንን ለመጨመር የሚያስችል ጥናት ማከናወኑንም ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ይህን ይፋ ያደረገው ዛሬ በተከናወነው የተፋሰሶች ልማት ከፍተኛ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው።

ዋና ዳይሬክተሯ በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ በከፍተኛ አደጋ ላይ የሚገኘው የአብያታ ሃይቅ ከዝዋይ ሃይቅ ጋር በቡልቡላ ወንዝ አማካኝነት የተሳሰረ ነው።

በመሆኑም የአዋሽ ወንዝ በክረምት ወራት የሚያጠቃውን ጎርፍ ወደ ዝዋይ ኃይቅ በማስገባት በቡልቡላ ወንዝ አማካኝነት አብያታ እንዲደርስ ለማድረግ የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት እየተከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።

እቦንጭ አረም ከአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች በተጨማሪ በስምጥ ሸለቆ ኃይቆች እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን መከላከል የሚያስችል አገር አቀፍ ስትራቴጂ ተነድፏል ብለዋል።

ስትራቴጂው በተለያዩ የምክክር መድረኮች እንዲተች ተደርጎ ወደትግበራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በተያያዘ ዜና በጨዋማነት የሚታወቀውን የበሰቃ ሃይቅ ለልማት ለማዋል ሶስት ፓኬጆችን የያዘ ጥናት ተከናውኗል ብለዋል።

በሃይቁ ዳር ጸሃይን በመጠቀም የተወሰነውን ሃይል ለማህበረሰቡ ማቅረብ፤ የቀረውን የውሃውን ጨዋማነት እንዲያስወግድ በማድረግ ለመተሃራ ከተማና አካባቢዋ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማቅረብ ደግሞ በፓኬጁ የተካተተ ጥናት መሆኑን አውስተዋል።

የበሰቃ ሃይቅን መጠን ለመከላከል እስካሁን ባለው ሂደት የተወሰነው የውሃው መጠን  ክረምት ላይ ብቻ ወደ አዋሽ ወንዝ እንዲፈስ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ጥናት ገቢራዊ ሲሆን ይህንን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም