የአዲስ አበባ ጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ሻምፒዮና በኢንስትራክተር ከበደ ሙሉጌታ ስም እንደሚካሄድ ተገለጸ

68

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2011 የአዲስ አበባ ጠረጴዛ ቴኒስ ዓመታዊ የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በኢንስትራክተር ከበደ ሙሉጌታ ስም እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ሊቀመኳስ አየለ ለሶስት ወራት ያህል በሚቆየው በዚህ ውድድር ሶስት ክለቦችና ስምንት ቡድኖች ይካፈሉበታል ብለዋል።

ውድድሩ በኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ትልቅ ታሪክ ባለቸው ኢንስትራክተር ከበደ ሙሉጌታ ስም የሚካሄድ ሲሆን በመጪው ቅዳሜ  በአራት ኪሎ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል እንደሚጀመር ነው የተናገሩት።

የፌዴሬሽኑ ዓመታዊ ውድድር የሆነው ይህ ሻምፒዮና ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ለሶስት ወራት ያህል የሚቆይ ሲሆን በአዲስ አበባ የተለያዩ የስፖርት፣ ትምህርትና ስልጠና መስጫ ማዕከላት የሚደረግ ይሆናል።

ኢንስትራክተር ከበደ ሙሉጌታ በህይወት ሳሉ ለአገሪቱ ጠረጴዛ ቴኒስ እድገት ሲሰሩ የነበሩና በአሰልጣኝነትና በብሄራዊ ቡድን ተጫዋችነት  አገራቸውን ወክለው መሳተፍ የቻሉ ሰው ናቸው።

ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ከ10 ዓመት በላይ በተጫዋችነት ከዚያም በኋላ በአሰልጣኝነት እስከ 2004 ዓ.ም አገልግለዋል።

በ1966 ዓ.ም በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ በተደረገው የግል የበላይነት የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ላይ ተካፍለው ሜዳሊያ ማምጣት የቻሉ ሲሆን ከተጨዋችነት በኋላ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ተተኪዎችን በማፍራት ይታወቃሉ።

በአዲስ አበባ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ውስጥ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ያገለገሉ ሲሆን ባሳለፍነው መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም