እሁድ በሚደረገው የጽዳት ዘመቻ ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

94

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2011 በመጪው እሁድ በሚደረገው የጽዳት ዘመቻ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋጽዎ እንዲያበረክት የተለያዩ ተቋማት ጥሪ አቀረቡ።

ሚያዚያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደውን አገራዊ የጽዳት ዘመቻ ንቅናቄ አስመልክቶ የትምህርት፣ የባህልና ቱሪዝምና የጤና ሚኒስቴሮች እንዲሁም የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መግለጫ ሰጥተዋል።

የትምሀርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ "መማር ራስን መለወጥ ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና በአገሪቱ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የጽዳት ዘመቻ ያደርጋሉ።

በዚህም 28 ሚሊዮን ተማሪዎችና 670 ሺህ መምህራን ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ የጽዳት ዘመቻውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ከዘረኝነት፣ ከቂምና ከአላስፈላጊ አስተሳሰቦች መጽዳት ያስፈልጋል'' በማለት “ዘረኝነትን ከውስጣችን ቆሻሻን ከአካባቢያችን ማፅዳት ይገባናል'' ብሏል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ''ዘረኝነት ቆሻሻ ነው፤ እናቃጥለው፤ እንቅበረው'' የሚል መልዕክትን ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት የምናሰማበት ይሆናል'' ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ የጽዳት ዘመቻውን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት ዘመቻው ዘላቂነት እንዲኖረው ተቋማት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

የጽዳት ዘመቻው የአካባቢን ጽዳት ከመጠበቅ ባለፈ መጥፎ ስሜትን አስወግዶ መልካም ስሜት ለማጎናፀፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጿል።

ዘመቻው ቀደም ሲል በሚኒስቴሩ በሃይጂንና በሽታ መከላከል የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠልና የአካባቢ ጽዳትን ባህል አድርጎ ለማስኬድ የሚያስችል ትልቅ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብሏል።

የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የጽዳት ዘመቻውን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደጠቆመው፤ ቱቦዎችና ቦዮች በደረቅ ቆሻሻ ከተደፈኑ የክረምቱ ዝናብ ሲመጣ የአካባቢ ብክለትን አባብሰው ችግር እንዳያስከትሉ መስራት አለበት።

በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ችግሩን ለመከላከልና ለማስቀረት እንዲሰራ ጥሪ አስተላልፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገር አቀፍ ደረጃ በመጪው እሁድ ከማለዳው 12 ሰዓት ከ30 እስከ ሁለት ሰዓት ቆሻሻን ከአካባቢ በመጥረግ በጽዳት ዘመቻ እንዲሳተፍ፤ ሁሉም ዜጋ ከአዕምሮው መጥፎና ክፉ ሃሳብን በማስወገድ መልካም አስተሳሰብን መተካት እንዳለበትም መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት ዘመቻውን ለማካሄድ ተቋማት ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ቀደም ሲልም ህዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከቆሻሻ የፀዳች ትሆን ዘንድ "እኔ አካባቢዬን አፀዳለሁ እናንተስ?" በሚል መሪ ሃሳብ ከተማ አቀፍ የጽዳት ንቅናቄ በአዲስ አበባ መጀመሩ ይታወሳል።

የጽዳት ንቅናቄው ሲጀመርም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊዎች ነበሩ።

ንቅናቄው በወሩ የመጨረሻ እሁድ ከህዳር እስከ ጥር ለሶስት ወራት ከተካሄደ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት መቋረጡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም