ተማሪዎች የሰላም አጋር እንጂ የጸጥታ ስጋት ሊሆኑ አይገባም....የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር

74

ደሴ ሚያዝያ 3/2011 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሰላም አጋር እንጂ የጸጥታ ስጋት ሊሆኑ አይገባም ሲሉ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ገለጹ።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በበኩላቸው ተረጋግቶ ለመማር መንግስት ሰላምና ደህንነታቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው መልሶ ያገረሸውን የጸጥታ ችግር ለማስተካከል በየደረጃው የሚደረገው ውይይት እንደቀጠለ ነው፡፡

ሚያዚያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ የነበረው ግጭት በአሁኑ ወቅት በአንጻራዊነት ቢረጋጋም ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም አለመመለሱ ተመልክቷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የሰላም አጋር እንጂ የጸጥታ ስጋት ሊሆኑ እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡

በትናንሽ ችግሮች ላይ በማተኮር ትልቁ የህዝብ ችግር እንዳይፈታ እንቅፋት መሆን እንደሌለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ተማሪዎች በአንድነትና በመቻቻል የመጡለትን ዓላማ አሳክተው አገርና ቤተሰብን በሙያቸው ማገልገል እንጂ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

አለመግባባቶች ሲኖሩ እንደ ምሁር በውይይት ሰከን ብሎ በመፍታትና ለእያንዳንዱ ጉዳይ ምክንያታዊ በመሆን የህግ የበላይነት እንዲከበር የድርሻቸውን እንዲወጡም መክረዋል፡፡

"የመማር መስተማር ሂደቱ ጤናማ እንዲሆን መደማመጥን ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉ ይገባልም" ብለዋል፡፡

መማር የማይፈልጉና እርስ በርስ በብሔርና በሃይማኖት ለመከፋፈል የሚጥሩ ተማሪዎችና መምህራንን ካሉ አጋልጠው በመስጠት ከመንግስት ጎን እንዲቆሙም አሳስበዋል፡፡

ክልሉ ችግር ፈጣሪዎችን በመለየት የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ፈንታሁን ጌትነት በበኩሉ በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር የመማር ማስተማር ሥራው መስተጓጎሉን ገልጿል፡፡

መንግስት በቂ የጸጥታ ኃይል በማሰማራት በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመታደግ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ጠይቋል፡፡

የችግሩ መንስኤዎች የግል ጥቅም ፈላጊ መምህራንና ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጾ " የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ችግር ፈጣሪዎች ተለይተው በህግ እንዲጠየቁ ይገባል" ብሏል።

" የጸጥታ ችግር ስጋቶችን አስቀድመን ለዩኒቨርሲቲው ብናሳውቅም ቅደመ ጥንቃቄ ባለመድረጉ በንብረትና በሰው ላይ ጉዳት ደርሷል" ያለው ደግሞ ተማሪ አየለ ባለው ነው፡፡

"በውስጣችን ያሉ የፖለቲካ ቅጥረኞችና የተለየ አጀንዳ በሚያራግቡ ተላላኪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ባለመወሰዱም ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል" ሲል ተናግሯል፡፡

የደሴ ከተማ ጸጥታና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ጸጋዬ በበኩላቸው በተፈጠረው አለመግባባት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ከሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ግቢ የጸጥታ ኃይል ገብቶ የማረጋጋት ሥራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

"የኢትዮጵያ ህዝብ ለተማሪዎቹ የጣለብንን አደራ በመወጣት ሰላምና ደህንነታቸውን እናረጋግጣለን" ሲሉም ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በአካባቢው ተፈጥሮ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ከትናንት ወዲያ ከሰዓት በኋላ ሰልፍ ለመውጣት ባደረጉት ሙከራ ግጭት መፈጠሩ ይታወሳል።

የተፈጠረው አለመግባባት ለአንድ ሰው ሞት፣ ለአራት ሰዎች የአካል ጉዳትና ለንብረት መውደም ምክንያት መሆኑም ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም